የክልል አደረጃጀትን ለመወሰን እየተካሄደ የሚገኘው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ የዴሞክራሲ ስርዓት ባህልን የሚያጎለብት ነው- የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር

36

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2015 የክልል አደረጃጀትን ለመወሰን እየተካሄደ የሚገኘው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ የዜጎችን ተሳትፎና የዴሞክራሲ ባህል የሚያጎለብት መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ይገዙ ገለጹ።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ይገዙ፤ በወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ ጋሌ ዋርጎ ቀበሌ በሚገኘው "ጋሌ ዋርጎ" የትውልድ አካባቢያቸው የኪንዶ ኮይሻ ምርጫ ክልል ምርጫ ጣቢያ "ሀ" ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተስፋዬ ይገዙ እንዳሉት፤ የክልል አደረጃጀትን ለመወሰን እየተካሄደ የሚገኘው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎና ልምምድ የሚያጎለብት ነው፡፡

የምርጫ ሂደቱ በሰላማዊ መልኩ እየተከናወነ በመሆኑ መራጮች ከማለዳው ጀምሮ ተሰልፈው ድምፅ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዴሞክራሲያዊ መንገድ የክልል አወቃቀርን ለመወሰን እየተካሄደ በሚገኘው ምርጫ ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኑን መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

የምርጫ ጉዳይ በካርድ ብቻ መወሰን እንዳለበት በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ በመያዙ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ ቀጥሏል ብለዋል።

ድምጽ ሲሰጡ ያገኘናቸው መራጮችም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልል አደረጃጀትን ለመወሰን እየተካሄደ በሚገኘው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ "ይጠቅመናል" በሚሉት አማራጭ ላይ ድምፃቸውን በነፃነት እየሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

በወላይታ ዞን 998 ሺህ 800 መራጮች ድምፅ ለመስጠት የመራጮች ካርድ የወሰዱ ሲሆን በ1 ሺህ 112 የምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳው ጀምሮ ድምጽ እየሰጡ ነው።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሥር በሚገኙ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የክልል አደረጃጀትን ለመወሰን ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም