‘ወርልድ ሪሶርስስ ኢኒስቲትዩት’ በአዲስ አበባ በተለያዩ መስኮች ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

251

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 29/2015 ‘ወርልድ ሪሶርስስ ኢኒስቲትዩት’ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም በአዲስ አበባ በተለያዩ መስኮች ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፉን እንደሚያደርግ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ከኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አኒ ዳሳጉፐታ እና የልዑካን ቡድናቸው ጋር በትብብር ልንሰራባቸው በምንችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል" ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።

የኢንስቲትዩቱ የአውሮፓ አስተባባሪ ቫን ቬልድሆን፣ የተቋሙ የአፍሪካ ዘርፍ አስተባባሪ ዋንጂራ ማታይ እና የአፍሪካ ቢሮ አስተባባሪ አክሊሉ ፍቅረሰላሴ(ዶ/ር) በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውንም አመልክተዋል።

በውይይቱም አጋርነትን በማጠናከር የሁለቱን አካላት ትብብር ወደ ስትራቴጂክ እና የተቀናጀ ደረጃ ለማሳደግና ኢንስቲትዩቱ የአዲስ አበባን ቀጣይ የልማት ስትራቴጂካዊ ፍኖት ለመንደፍ፣ የተቀናጀ መረጃን መሰረት ያደረገ የአመራር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመረጃ ቋት ለመገንባት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

በዋናነትም አዲስ አበባ የነገ ተስፋ የሆኑ ሕጻናትን በእንክብካቤ ለማሳደግና ለትውልድ ግንባታ የምትመረጥ ከተማ ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ ሁለገብ በሆነ መልኩ ለመደገፍ መስማማቱን ተናግረዋል።

‘ወርልድ ሪሶርስስ ኢኒስቲትዩት’ ላሳየው የትብብር ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ከንቲባዋ ምስጋና ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም