የህዝበ ውሳኔው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ቀጥሏል--የደቡብ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

46

አማሮ ኬሌ (ኢዜአ)ጥር 29/2015--የሚተዳደሩበትን ክልል ለመወሰን በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መቀጠሉን የደቡብ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በአማሮ ልዩ ወረዳ ኬሌ 01 ቁጥር 2 ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል።

ኃላፊዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት የህዝበ ውሳኔ ድምጽ እየተሰጠባቸው ባሉ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጡ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደቀጠለ መረጋገጡንም ተናግረዋል።

"ህዝቡ አኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅሜን ያረጋግጥልኛል ያለውንና የሚተዳደርበትን ክልል በራሱ ድምፅ የሚወስንበት ኩነት እንደመሆኑ በነቂስ ወጥቶ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እየተጠቀመ ነው" ብለዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ድምጹን የሚሰጠው ህብረተሰብ የሰልፍ ሥርዐት ከማክበር ጀምሮ ለሠላማዊና ነፃ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እያደረገው ላለው አስተዋጾ ወይዘሮ ሰናይት አመስግነዋል ።

የአማሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው "በልዩ ወረዳው 98 ምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉና ህብረተሰቡም ሰላሙን ጠብቆ ይበጀኛል ያለውን ውሳኔ በድምጹ እያረጋገጠ ነው" ብለዋል።

የሚተዳደሩበትን ክልል ለመወሰን እየተካሄደ ባለው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይ በልዩ ወረዳው የተዘመገቡ ከ109 ሺህ በላይ ዜጎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የወረዳው አስተዳደር ህዝበ ውሳኔው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከፀጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመናበብ ሠላማዊ ሂደቱን የማስቀጠል ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም አቶ ወገኔ አመልክተዋል።

በዛሬው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ በ3 ሺህ 771 የምርጫ ጣቢያዎች ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም