የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በጌዴኦ ዞን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጻቸውን ሰጡ

34

ዲላ ጥር 29/2015 (ኢዜአ) የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በጌዴኦ ዞን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጻቸውን ሰጡ።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጌዴኦ ዞን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ለህዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ድምጻቸውን ከሰጡት መካከል የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ ኮሬ በዲላ ዙሪያ ወረዳ በሚችሌ ሲሶታ ምርጫ ጣቢያ በመገኘት ነው ድምጻቸውን የሰጡት።

እንዲሁም በፌደሬሽን ምክር ቤት በሚኒስቴር ማእረግ የህገ መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ጸሃፊ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ በዲላ ከተማ ሃርሱ 03 ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰና የደቡብ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አበራ ክጴ በዲላ ከተማ ሀሴደላ 2 ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ለህዝበ ውሳኔው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

ከሚሽነር አበራ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ ታዝበዋል።

ህዝቡም በነቂስ ወጥቶ ድምጹን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱም ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ መሰረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም