የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በጂንካ ጣቢያ በመገኘት ድምጽ ሰጡ

170

ጂንካ፣ ጥር 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ እና የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በጂንካ አርክሻ "ለ" ንዑስ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል።

በጂንካ ከተማ በሚገኙ 24 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲና የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በጂንካ አርክሻ ''ለ'' ንዑስ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን ሰጥተዋል ።

ከማለዳው 12:00 ጀምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ እንዳለ መረዳት ችለናል ብለዋል።

ድምጽ የሚሰጠው ህዝብ ከሌሊቱ 10:00 ሰዓት ጀምሮ በመሰለፍ ድምፁን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ይህም ህዝቡ ህገመንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ስርዓቶች ህገመንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በተግባር ከመፈፀም አኳያ ከሚታዩ ክፍተቶች የተነሳ ህዝቡ በፍላጎቱ የሚሳተፍበት ዕድል እንዳልነበረ አንስተዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ እንዲወስን በተፈጠረው ዕድል የህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ተሳትፎው የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።

በዞኑ 428 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ የተናገሩት የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው በየጣቢያዎቹ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዞኑ በሚገኙ የድምጽ ጣቢያዎች ያለው ሰላማዊ ሁኔታ ሂደቱ ከስጋት ነፃ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸው፤ ከፀጥታ አኳያ ቀደም ብሎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በስፋት በመሰራታቸው ስጋትን ማስቀረት እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ህዝቡ በተሰጠው ህገመንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ተጠቅሞ ድምፅ እንዲሰጥ አቶ ንጋቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በደቡብ ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ እና ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ በአሁኑ ሰዓት ሕዝበ ውሣኔ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም