ቀጥታ፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው የሕዝበ ውሣኔ መራጮች ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉ--ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 29/2015 በደቡብ ብሔር ሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው የሕዝበ ውሣኔ መራጮች ድምጽ እየሰጡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ድምጽ የመስጠት ሒደቱ እየተከናወነ ያለው በክልሉ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ላይ መሆኑን ቦርዱ አመላክቷል።

ቦርዱ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ እያደረገ ባለው ክትትል በወላይታ ዞን፣ በበሌ የምርጫ ማዕከል፣ ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ የህግ ጥሰት መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡

በጣቢያው ድምፅ በመስጠት ሂደት ወቅት የቀበሌ አስተዳደር ሀላፊዎች ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ በመገኘት 105 የሚሆን የግለሰብ ጊዜያዊ መታወቂያዎችን በመያዝ ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ ዜጎች በማደል ህገ ወጥ ተግባር ላይ መሰማራታቸውን ቦርዱ ደርሶበታል።

በዚህ መሰረትም ሶርቶ ቀበሌ ሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ ላይ የተፈፀመው የህግ ጥሰት እስኪጣራ ድረስ ድምጽ የመስጠት ሂደቱ እንዲቋረጥ ቦርዱ ወስኗል፡፡

በቀጣይም ቦርዱ ተመሳሳይ የህግ ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ክትትል የሚያደርግ ሲሆን ተከስተው ሲገኙ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም