ቀጥታ፡

ለሕዝበ ውሣኔው ድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ተሠራጭቷል-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በነገው እለት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ-ውሳኔ ያሰጣል።

በዕለቱ በ ሕ ዝበ ውሣኔው ድምፅ መስጫ ቀን አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችን በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች አሠራጭቶ ማጠናቀቁን ቦርዱ አስታውቋል።

ቦርዱ ሥርጭቱን ያከናወነው በ31 ማዕከላት ሥር ባሉ 3 ሺህ 771 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑንም ገልጿል።

ከምርጫ ጣቢያዎቹ መካከል ሁለቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ብርብርና ቁጫ ላይ የተከፈቱ የተፈናቃይ ጣቢያዎች መሆናቸውን ቦርዱ አመላክቷል።

ሥርጭቱ የተከናወነው ከጥር 25 እስከ ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።

ምርጫ ጣቢያዎቹም በነገው ዕለት ለሚከናወነው የሕዝበ ውሣኔ የድምፅ መስጠት ሂደት በሙሉ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ ሲል ቦርዱ ገልጿል።

ጣቢያዎቹ በነገው ዕለት ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ክፍት የሚሆኑ ሲሆን፤ መራጮች በተጠቀሰው ሰዓት ወደ ተመዘገቡበት ጣቢያ በመሄድ ድምፃቸውን እንዲሰጡም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም