ነገ በሚካሔደው ህዝበ ውሳኔ ላይ ካርዳችንን በአግባቡ ለመጠቀም ተዘጋጅተናል--የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ነገ በሚካሔደው ህዝበ ውሳኔ ላይ ካርዳችንን በአግባቡ ለመጠቀም ተዘጋጅተናል--የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች
አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 ነገ በሚካሔደው ህዝበ ውሳኔ ላይ ካርዳቸውን በአግባቡ በመጠቀም የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ በአርባ ምንጭ ከተማ ቅኝት ባደረገባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለህዝበ ውሳኔው ምቹ እንዲሆኑ የምርጫ ቦታዎችን በማጽዳትና ድንኳን በመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማው ነዋሪዎች እንዳሉትም ድምጻቸውን በነጻነት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ ዳሬ ቀበሌ ነዋሪ የኔሰው ባለሞ በሰጡት አስተያየት ነገ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ የቀበሌው ነዋሪ ካርድ መውሰዳቸውን አስታውሰዋል።
ነዋሪው "የምንተዳደርበትን ክልል አወቃቀር ለመወሰን በተያዘው ዕቅድ ላይ የራሴን ውሳኔ ለማሳረፍ በነገው እለት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምጼን ለመስጠት ተሰናድቻለው" ብለዋል።
ህዝበ ውሳኔው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም የኔሰው አረጋግጠዋል።
ወጣት ብሩክ ተስፋ በበኩሉ ቀደም ሲል በተካሄደው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ምዝገባ በመመዝገብ ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ የራሱን ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ለህዝበ ውሳኔው ስኬታማነት መንግስትና ምርጫ ቦርድ ያደረጉት ቅደመ ዝግጅትና ያሳዩት ቁርጠኝነት አስደስቶናል የሚለው አስተያየት ሰጪው ይህም መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠቱን ያሳያል ብሏል።
የህዝብ ጥያቄ፣ መብትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተዳደሩበት ክልል አወቃቀር በሚወስነው ህዝበ ውሳኔ ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ ሾሌ ሜላ ቀበሌ ነዋሪው ሳሙኤል ሳኦል ናቸው።
የህዝበ ውሳኔው ሂደት እስከ አሁን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸው እስከ ፍፃሜው ድረስ በዚሁ መልኩ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ የሆስፒታል መንደር ምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈጻሚ ዝናሽ መስፍን በሰጡት አስተያየት በነገው እለት የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም በምርጫ ጣቢያው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል።
በተለይም ምርጫ ጣቢያውን ለመራጮች ምቹ ለማድረግ የምርጫ ቦታዎችን በማጽዳትና ድንኳን በመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በህዝበ ውሳኔው ምርጫ ለመሳተፍ በምርጫ ጣቢያው 1 ሺህ 164 መራጮች ተመዝግበው ካርድ መውሰዳቸውን ጠቁመው ሁሉም ካርዱን ሳያባክን ድምጹን እንዲሰጥም አሳስበዋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሕዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል።