ቀጥታ፡

በህዝበ ውሳኔው በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል-የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች

ጂንካ ጥር 28/2015 (ኢዜአ) በነገው ዕለት በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ላይ በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የጂንካ ነዋሪዎች ገለፁ።

ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት መደረጉንም የዞኑ ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነገ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሣኔ ይካሄዳል።

በዚሁ መሰረት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ነዋሪዎች እንዳሉት በህዝበ ውሳኔው በንቃት በመሳተፍና ድምጽ በመስጠት ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም ተዘጋጅተዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ታሪኩ መኮንን "ህዝበ ውሳኔው የራሴን ዕድል በራሴ የምወስንበት ልዩ አጋጣሚ ነው" ብለዋል።

"ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ከምናረጋግጥባቸው መንገዶች አንዱ የህዝበ ውሳኔ ነው" ያሉት አቶ ታሪኩ "ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ህገ-መንግስታዊ መብቱን መጠቀም አለበት" ብለዋል።

"በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ገረሱ ቢሆኔ ናቸው።

ስለህዝበ ውሳኔው ግንዛቤ ሲሰጥ መክረሙን የጠቆሙት አቶ ገረሱ ባገኙት ግንዛቤ ነገ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በድምጽ መስጫ ጣቢያ በመገኘት ውስኔያቸውን ለማሳወቅ መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል።

"እኔም ባለቤቴም በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የሚያስችለንን ካርድ በመውሰድ የተሰጠንን መብት ለመጠቀም ተዘጋጅተናል" ያሉት ደግሞ ዋና ሳጂን ዘውገ ኃይሉ ናቸው።

"የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ህዝቡ በህዝበ ውሳኔው በመሳተፍ በህገ-መንግስቱ የተደነገገ መብቱን ተግባራዊ ማድረግ አለበት" ብለዋል።

"ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል" ያሉት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሸጎሌ ሾዴ ናቸው።

በዞኑ በሚገኙ 428 የምርጫ ጣቢያዎች የህዝቡንና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ደህንነት የሚያስጠብቁ የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ኮማንደር ሸጎሌ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም