ቀጥታ፡

በኢሉባቦር ዞን የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 19 ሺህ ሄክታር የቡና ተክል ዕድሳት ስራ እየተሰራ ነው

መቱ (ኢዜአ) ጥር 28/2105 ለቡና ተክል ዕድሳት ስራ ትኩረት በመስጠት እና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን የኢሉባቦር ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

በተያዘው ዓመት ከ19ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ የቡና ተክልን በጉንደላና በንቅለ ተከላ ለማደስና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ነው። 

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ያረጁና ምርታማነታቸዉ የቀነሰ የቡና ተክሎችን በመጎንደል እንዲሁም ነቅሎ በአዲስ ችግኝ በመተካት ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

አቶ ናስር ሱሌማን ከዚህ ቀደም ካረጁ የቡና ተክሎቻቸዉ የሚያገኙትን መጠነኛ ምርት ላለማጣት የቡና ተክሎቹን ለመጎንደል ወይም ነቅሎ በአዲስ ለመተካት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ያነሳሉ። 

ነገር ግን በግብርና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ባገኙት ትምህርት እንዲሁም ከሌሎች አርሶ አደሮች ልምድ በመውሰድ አሁን ካላቸው ያረጁ ተክሎች ከፍለው በመጎንደል ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። 

አቶ እንግዳ ሞሲሳ በበኩላቸው የቡና ተክሎች እያረጁ ሲሄዱ ምርታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለሚቀንስ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዙ መጎንደል ያለበትን በመጎንደል ተነቅሎ በሌላ የሚተካውን ደግሞ ነቅለዉ በአዲስ የመተካት ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ይናገራሉ። 

ከ19ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ከሚገኝ የቡና ተክል መካከል 14ሺህ ሄክታሩ በጉንደላ፤ 5ሺህ ሄክታር ደግሞ በንቅለ ተከላ የሚታደስ መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ አበበ ተፈሪ ለኢዜአ ተናግረዋል። 

የቡና ተክል ዕድሳት ስራ ዋነኛ ዓላማ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር አርሶ አደሮቹም ሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።

የቡና ተክሎች እያረጁ ሲሄዱ ምርታማነታቸው እየቀነሰ የሚሄድ ሲሆን በጉንደላ ወይም በንቅለ ተከላ የታደሰ ቡና ምርታማነቱ የሚጨምር መሆኑንም ነው አቶ አበበ የገለጹት። 

በዞኑ በአጠቃላይ 261ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ መሆኑንና ከዚህ ውስጥም 140ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘዉ ቡና ያረጀና ዕድሳት የሚፈልግ መሆኑ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም