ሴኔጋል የሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ውድድር ዋንጫ አሸናፊ ሆነች

46

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 28/2015 ሴኔጋል አልጄሪያን በመለያ ምት በመርታት የሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ዋንጫ አሸናፊ ሆናለች።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ትናንት ተጠናቋል።

በአልጄሪያ ኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል አዘጋጇን አልጄሪያን በመለያ ምት 5 ለ 4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እና በተጨማሪ 30 ደቂቃ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት ተሸጋግረዋል።

በተሰጠ የመለያ ምትም ሴኔጋል 5 ለ 4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ አንስታለች።

የአልጄሪያው የአማካይ መስመር ተጫዋች ሁሴም ምሬዝጊ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

ሌላኛው አልጄሪያዊ አይሜን ማሂኡስ በአምስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሽልማትን አግኝቷል።

የሴኔጋል አሰልጣኝ ፓፔ ታው ኮከብ አሰልጣኝ እንዲሁም የሴኔጋል ግብ ጠባቂ ፓፔ ማማዱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆነው ተመርጠዋል።

ሴኔጋል የቻን ውድድር የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማትንም አግኝታለች።

በተጨማሪም የሴኔጋሉ ላሚን ካማራ የፍጻሜው ጨዋታ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም