የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ማዕከሉ በዘርፉ ያለውን የስልጠና ተደራሽነት የሚያሰፋ ነው - ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው

56

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 27/2015 የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የሐዋሳ ማሰልጠኛ ካምፓስ በዘርፉ ያለውን የስልጠና ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ በቀጣይ ሌሎች የማሰልጠኛ ማዕከላትን የመገንባት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው ሀዋሳ አቪዬሽን ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።

የአገልግሎት ፍላጎት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ የአቪዬሽን አካዳሚው በሀዋሳ ሁለተኛ ካምፓሱን መክፈቱን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

ካምፓሱ አየር መንገዱ የሰነቀውን ራዕይ እውን ለማድረግ የላቀ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

የስልጠና ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለው ካምፓስ በአቪዬሽን ዘርፍ በርካታ ሙያተኞችን እንደሚያሰለለጥን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ እና ዛሬ በተመረቀው የአቪዬሽኑ ማሰልጠኛ ማዕከል የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎችን የማሰልጠን ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ካሳዬ ይማም፤ በአየር መንገዱ የስኬት ጎዳና የአቪዬሽን መስኩ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የሐዋሳው የስልጠና ማዕከል ለቀጣይ የስኬት ምዕራፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማዕከሉ በሐዋሳ መገንባቱ ለከተማዋ ዘርፈ- ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ወደ ሐዋሳ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መምጣቱንና ይህም የከተማዋን የቱሪዝም ፍሰት የማሳደግ ፋይዳ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ዛሬ የተመረቀው የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የሀዋሳ የስልጠና ማዕከል በአንድ ጊዜ 320 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚችል ተገልጿል።

የስልጠና ክፍሎቹ 3 የምስለ በረራ ማሳያዎች(ሲሚዩሌተር)፣ 3 አውሮፕላኖችን ለመጠገን የሚያስችል ሕንጻዎች(ሀንጋሮች) እና 4 የኮምፒዩተር ክፍሎች አሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ77 ዓመታት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የአቪዬሽን የሥልጠና ማዕከሉ ደግሞ ላለፉት 65 ዓመታት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

አየር መንገዱ በአዲስ አበባ በሚገኛው ዋናው የአቪዬሽን አካዳሚ የፓይለት፣ የአውሮፕላን ጥገና፣የበረራ መስተንግዶ፣የምግብ ዝግጅትና ሌሎችንም ስልጠናዎችን ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም