በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው- የዘርፉ ምሁር

37

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2015 በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ የዘርፉ ምሁር ገለጹ።

በአንድ አገር ለተሻለ ማህበረሰብ ግንባታና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ከምንም በላይ የማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናል።


በሳይንስና ምርምር፣ በህክምናም ይሁን በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች በትምህርት የሚደገፍ እውቀት ለአንድ አገር የስኬት ጉዞ መሰረት የሚጥል መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።


በመሆኑም በኢትዮጵያ የትምህርት ስርአት የነበረውን ስብራት በመጠገን በተሻለ መልኩ የዘርፉን ጥራት ለማስጠበቅ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ባህል ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሰ ጃለታ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሰ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የልማትና እድገት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለነበሩ ስብራቶች መፍትሄ ለመሻት የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮው ዓመት በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ የነበረውን የተቀናጀ ስራ በምሳሌነት አንስተዋል።


የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ መስራት ይገባል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ታደሰ፤ በተለይ በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ከቤተሰብ ጀምሮ የትምህርት ማህበረሰቡ ለለውጥ በጋራ መስራት አለበት ብለዋል።


ለመምህራን ተከታታይነት ያለው የብቃት ማሳደጊያ ስልጠና መስጠትም ሊታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።


ከዚህ ቀደም የነበረው የመምህራን ስልጠና ከጥራትና ተደራሽነት አንፃር ችግር እንደነበረበት አስታውሰው አሁን ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም