የካንሰር ህመም በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ዜጎች አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የካንሰር ህመም በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ዜጎች አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27 ቀን 2015 የካንሰር ህመም በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ዜጎች አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
ዓለም አቀፍ የካንሰር ህሙማን ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር ህመም በየቀኑ ከ27 ሺህ በላይ በየሰዓቱ 1ሺህ 141 ሰዎች እንደሚሞቱና፤ በገዳይነቱ ከልብ ህመም ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡
በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች በካንሰር ህመም ይያዛሉ ከነዚህ ውስጥም በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው 70 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ የሆኑት ዶክተር ኩኑዝ አብደላ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከልብ ህመም ቀጥሎ ካንሰር በገዳይነቱ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በኢትዮጵያ የበሽታው ገዳይነት እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ህመሙ በጊዜው ህክምና ካገኘ መዳን የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ በማሳደግ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ካንሰር ያሉ ህመሞችን በመከላከል ረገድ እየተሰራ ቢሆንም አሁንም የበለጠ አጠናክሮ መቀጠልን ይጠይቃል።
የካንሰር ህመም አምጪ ምክንያቶችን አስቀድሞ በመከላከል ህመሙ ሳይሰራጭ ከተደረሰበት ሊድን የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም የካንሰር ህመም በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ዜጎች በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ መከላከል ላይ ማተኮር አለባቸው።
በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል አመጋገብን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወንዱ በቀለ በበኩላቸው፤ የቀኑ መከበር ዋና ዓላማ ህብረተሰቡ በካንሰር ላይ ያለው ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ 'ካንሰር የፈጣሪ ቁጣ ነው ፤ህመሙ ከያዘ አይለቅም እና የመሳሰሉትን የተዛቡ እና የተሳሳቱ መረጃዎች በማስወገድ አስቀድሞ መከላከል አለበት' ብለዋል፡፡
ቀኑን ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባባር በውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።