በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ሂደት ቅንጅታዊ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

32

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27/2015 በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ሂደት ቅንጅታዊ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በምክር ቤቱ የጤና ማኅበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማኅበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በሴቶች መብትና ሁለንተናዊ ደህንነነት በማስጠበቅ ሂደት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

የሴቶች ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ለተደራጁ በርካታ ማኅበራት ተቋማዊ ብቃታቸውን ለማጎልበት የቴክኒክና ሙያዊ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ለጥቃት የተዳረጉ ሴቶችና ሕፃናትን የተሀድሶ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፎች መደረጋቸውንም አስታውሰዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ጥቃቶች ለተፈፀሙባቸው 1 ሺህ 357 ሴቶች የተሀድሶ አገልግሎት መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስትሯ ከዚህ ውስጥ ለ369 ሴቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የመከላከልና የችግሩን አስከፊነት በማስተማርም ብዙ መሰራቱን አስታውሰው በዚህም ተጨባጭ ውጤት ታይቶበታል ብለዋል።

በሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት አድራሾች ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግም ከፍትሕ ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ለመከላከል በአዲስ አበባ በ119 ወረዳዎች በሚገኙ 650 ብሎኮች ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማሰጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

በሌሎች ክልሎችም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የቅንጅት ስራዎች እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በጎዳና ላይ ውሎና አዳራቸውን ያደረጉ ከ23 ሺህ በላይ ሕፃናትን በማንሳት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት ተችሏል ብለዋል።

ከፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ተይዘው በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ፤ ሚኒስቴሩ የክልሎችን መዋቅር ይዞ በሪፖርቱ ገምግሞ መምጣቱ መልካም መሆኑን አድንቀዋል።

የክልሎችን ጥረት ለማገዝ የሚያደርገው ድጋፍና እገዛም በበጎ ጎን የሚታይ በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ሂደት ቅንጂታዊ ጥረቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዚህ ባለፈ ዜጎችን ከጎዳና ህይወት በማውጣት በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በማድረግ ሂደት ብዙ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም