ቀጥታ፡

የፖሊስ አመራርን በዕውቀትና በአመለካከት በመገንባት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

ደብረ ማርቆስ ( ኢዜአ) ጥር 27/2015. የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በየደረጃው የሚገኘውን የፖሊስ አመራር በዕውቀትና በአመለካከት በመገንባት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ለአንድ ዓመት በፖሊስ አመራርና ቴክኒክ ሳይንስ ያሰለጠናቸውን የአንደኛ ዙር ልዩ ሰርተፊኬት እጩ መኮንኖችን ዛሬ አስመርቋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ፖሊስ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የማይተካ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ አዲስ የፖሊስ ኃይል በማፍራት፣ አሰራርን በማዘመንና የአመራሩን አቅም በመገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት ፈጣንና ተለዋዋጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ የሚችል ፖሊሳዊ ዕውቀትና ጥበብን የተላበሰ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህም የወንጀል ስጋቶችን አጥንቶ በመለየት፣በመተንተን ቀድሞ ለመከላከልና ፈጥኖ ለመቀልበስ የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባም አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት በዕውቀት፣ በአመለካከትና በሥነምግባር የታነፀ የፖሊስ ኃይል እና ዘመኑን የዋጀ አመራርን በማፍራት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው አለሜ በበኩላቸው በክልሉ የተረጋጋ ፀጥታና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የፖሊስ አመራር ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ለዚህም ኮሌጁ ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን አወዳድሮ በፖሊስ አመራር ሙያ አሰልጥኖ ዛሬ ማስመረቁን ተናግረዋል።

ተመራቂዎችም ለአንድ ዓመት በፖሊስ አመራር፣ የፖሊስ ሳይንስና የአካል ብቃት ስልጠናዎችን በብቃት የተወጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

አክለውም ተመራቂ የፖሊስ አመራሮች በስልጠናው የቀሰሙትን ዕውቀት ተጠቅመው አዳዲስ አሰራሮች በመዘርጋት፣ ስምሪትን በማቀድ፣ በማደራጀትና በመምራት ችግሮችን ፈጥነው ለመፍታት የሚያስችል አቅም የገነቡ ናቸው ብለዋል።

በሚመደቡበት አካባቢ ከነባር አመራርና አባላት ጋር በመቀናጀት ለክልሉም ሆነ ለሀገር ሰላም ተግተው በመስራት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አሳስበዋል።

በጋዜጠኝነትና ተግባቦት የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዛ ወደ ፖሊስ አመራር ስልጠና መግባቷን የገለጸችው ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል ረዳት ኢንስፔክተር አይናለም ወርቁ ነች።

ለሙያው ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት በመጠቀም ፍትህ የሚፈልገውን ህዝብ በቅንነት፣ በታማኝነትና በፍትሃዊነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም