በባቡር መሰረተ ልማት ላይ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል- የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር

165

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 27 ቀን 2015 የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር፤ በባቡር መሰረተ ልማት ላይ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን አስታወቀ።

የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መሠረተ ልማት ላይ በተደጋጋሚ ዘረፋና ስርቆት ተፈፅሞባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ተዘዋውረው እየጎበኙ ነው።

የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ፤ በመሠረተ ልማቱ ላይ በተደጋጋሚ በሚፈፀም ዘረፋ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍተኛ ዘረፋና ስርቆት እየተፈፀመበት ፈተና እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የወጪ እና ገቢ ምርቶችን በፍጥነት በማጓጓዝ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ አገልግሎቱን እያፋጠነ ቢሆንም በየጊዜው የሚፈፀምበት ስርቆት እንቅፋት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጉብኝት በተደጋጋሚ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት በጋራ ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።

በጉብኝቱ የባቡሩ መስመር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ ለችግሩ የጋራ መፍትሄ የማምጣት አላማ እንዳለውም ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ እና ሌሎችም የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የወጪ ንግድ ሎጂስቲክስን በማሳለጥ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል።

እየተገባደደ ባለው የጥር ወር ብቻ እንኳን ከ350 ሚልየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም