ከመላው አፍሪካ ሀገራት ለሚመጡ ሙያተኞች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ አየር መንገድ

33

ጥር 27/2015 ( ኢዜአ) ከመላው አፍሪካ ሀገራት ለሚመጡ ሙያተኞች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀዋሳ ያስገነባውን የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ በተገኙበት አስመርቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአየር መንገዱ የአገልግሎት ፍላጎት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ የስልጠና ማእከሉ መገንባቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጽያ አየር መንገድ ለረዥም አመታት በአዲስ አበባ ከነበረው የአቪዬሽን ማዕከል ቀጥሎ የሀዋሳው ማዕከል እንደ ሀገር 2ተኛ ነው ብለዋል።

የማሰልጠኛ ተቋሙ በ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የስልጠና ማዕከሉ በውስጡ 320 ተማሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የመማሪያና የማደሪያ ክፍሎች፣ የመመገቢያ ካፍቴሪያዎችና ሌሎችም ለስልጠናው ማዕከል ግብአት የሚሆኑ ዘመናዊ መሳሪያዎች ያሟላ መሆኑን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም ዙሪያ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰንቆ ኢትዮጵያን ለአለም እያስተዋወቀ ያለ ስመ ጥር አየር መንገድ ነው ብለዋል።

ሁለተኛውን የአቪዬሽን የስልጠና ማዕከሉንም በሀዋሳ መገንባቱ ለአየር መንገዱም ሆነ ለከተማዋ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እንደሚያስገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ77 አመታት የአየር ትራንስፖርት በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የአቬዬሽን የስልጠና ማዕከሉ ደግሞ ላለፉት 65 አመታት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

አየር መንገዱ እ. ኤ.አ በ2016 የአዲስ አበባ የስልጠና ማዕከሉን ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የማስፋፊያና እድሳት ማደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም