የማይቀለበሰው የሰላም ጉዞ አዳዲስ ለውጦችን እያስመዘገበ ይቀጥላል- ዶክተር አብርሃም በላይ

56

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 27/2015 “የማይቀለበሰው የሰላም ጉዞ፤ አዳዲስ ለውጦችን እያስመዘገበ ይቀጥላል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት በሐላላ ኬላ ተገናኝተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በተጨባጭ በተመዘገቡ ውጤቶች መሰረት፣ በትግራይ ክልል ያለውን የሰላም ፣ የደህንነት እና የመሰረታዊ አቅርቦቶችን በዘላቂነት የማስፋት ጉዳይ ተጨማሪ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

በቀጣይ ቀናት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት ተጨማሪ ዕለታዊ በረራዎችን መጨመርና የየብስ ትራንስፖርትን ከአስተማማኝ የጸጥታና ደህንነት ዝግጅት ጋር በማቅረብ፤የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ ስራ ለመስራት ምክክርና ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም በትግራይ የባንክ ቅርንጫፎች የተስተዋለውን የገንዘብ ፍሰትና አቅርቦት ለማሻሻል ተጨማሪ እርምጃዎች ተወስደዋል ያሉት ሚኒስትሩ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን በፍጥነት ለማስቀጠል የሚያግዝ ሁኔታም በመፍጠር ላይ ይገኛል ብለዋል።

“የማይቀለበሰው የሰላም ጉዞ፤ አዳዲስ የማጠናከርያ እመርታዎችን ማስመዝገቡን ይቀጥላል” ሲሉም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም