ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በአገር ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመግታት ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

41

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 26/2015 -- ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በአገር ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመግታት ተቋማዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ አስገነዘቡ።

ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ላይ ያተኮረ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አማካኝነት የሚዘጋጀው 'ጉሚ በላል' የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በአገር ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።

"ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ዝውውር ኢኮኖሚን ይጎዳል፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያቀጭጫል፣ ምርቶች ወደ ውጪ እንዳይላኩ እንቅፋት ይሆናል " ሲሉ አብራርተዋል።

ችግሩ በአገር ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ተጽእኖ አንጻር ዘርፉን በአግባቡ አውቆ መምራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ተጠያቂነትና ቅንጅታዊ አሰራርን መተግበር እንደሚገባም አመልክተዋል ።

"ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በአብዛኛው በረቀቀ መንገድ የሚከናወን እንደመሆኑ ችግሩን ለመግታት ጠንካራ ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል " ሲሉም አክለዋል።

ጠንካራ ተቋም ሲገነባ በማንኛውም መልኩ የአገር ጥቅምንና የዜጎች መብትን የሚያጓድሉ ተግባራትን መግታት እንደሚቻል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ እቅድ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ታደለ በበኩላቸው በክልሉ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ ቢሆንም ሕገ ወጥነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላከቱ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ 521 ሚሊዬን ብር ግምት ያላቸው በሕገ ወጥ ንግድና በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ምርቶች መያዛቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 228 ነጥብ 2 ሚሊዬን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ሕገ ወጥ ምርቶች መያዛቸው ጠቅሰው "ችግሩ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አመላካች ነው" ብለዋል።

በሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ 120 ነጋዴዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉና 869 መጋዘኖች መታሸጋቸውንም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ወጥነት ያላቸው ሕጎች፣ ደንቦችና አሰራሮችን እየተገበረ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ችግሩን ለመግታት የተቀናጀና ወጥነት ያለው እርምጃ የሚያስፈልግ መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው ።

"በተለይም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመግታት የተቋቋሙ ኬላዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ኬላ ጠባቂዎች በምን መልኩ ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ አለበት" ሲሉ ጠቁመዋል።

የኮንትሮባንድ መተላለፊያ የሆኑ ኮሪደሮችን ለይቶ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም ቅድመ መከላከል ስራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ተሳታፊዎቹ ችግሩ የሁሉም እንደመሆኑ ሕዝቡም ከመንግስት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ትብብርና ጥረት ማድረግ አለበት" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም