ቀጥታ፡

በጦርነት ጉዳት የደረሰበት 1 ሺህ 561 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 በጦርነት ጉዳት የደረሰበት 1 ሺህ 561 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች መልሶ በመገንባት ሂደት ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

መሰረተ ልማቶንቹን ለመጠገን ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለአገልግሎት ዝግጁ በማድረግና የማስተላለፊያ መስመሮችን በመጠገን ስራ ለማስጀመር ዋጋ የተከፈለበት ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ 1 ሺህ 561 ኪሎ ሜትር የከፍተኛ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመጠገን ታቅዶ 1 ሺ 561 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የከፍተኛ ሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና መከናወኑን ተናግረዋል።

በተሰሩ ስራዎች ካለፈው ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ታህሳስ መጀመሪያ ድረስ ኤሌክትሪክ ማግኘት የሚችሉበትን ሰፊ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በወልድያ መውጫ "ዶሮ ግብር" አካባቢ የሚገኘው ማከፋፋያ ጣቢያ ተነቅሎ የተወሰደ በመሆኑ ጣቢያውን ለመተካት እንደ አዲስ ስራው መከናወኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ከማከፋፈያ ጣቢያ ሃይል ሲያገኙ የነበሩ የተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሃይል እንዳላገኙ አስረድተዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው 15 እና በ33 ኪሎ ቮልት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የ15 ኪሎ ቮልት መስመሮች በሙሉ ዝግጁ ሆነው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

ቀሪውን የ33 ኪሎቮልትን ለአገልግሎት ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በምዕራብና ምስራቅ በኩል ያሉትን አካባቢዎች እኩል በመጠገን በትግራይ፣ አማራና አፋር ያለውን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው ።

ተቋሙ በነዚህ አካባቢዎች የደረሰው የመሰረተ ልማት ጉዳት ለመጠባበቂያ የተቀመጠውን መለዋወጫዎችን ጭምር ተጠቅሞ የመልሶ ጥገና ስራውን ለማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የወጡትን መለዋወጫዎች ለመተካት 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ሃላፊው አስገንዝበዋል።

ሁሉም የመስተዳድርና የህብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ወጪ ለተጠገኑ የመሰረተ ልማቶች ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም