ጠንካራ አንድነት - ለዘላቂ ሰላም መሰረት!

1321

በእንግዳው ከፍያለው (ባህር ዳር ኢዜአ)

በረጅም እንጨት ጫፍና ጫፍ በገመድ ታስረው የተንጠለጠሉ ቋጠሮዎችን ተሸክማ ከጓደኞቿ ጋር ገበያ እየሄደች ነበር የተገናኘነው። ወጣት ማሪማ ሜካ ትባላለች፤ ዕድሜዋ ከሃያ ዓመት አያልፍም። በእንጨቱ አንደኛው ጫፍ 10 ሊትር አረቄ የያዘ ጀሪካን፤ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ሌላ ቋጠሮ በማንጠልጠል ተሸክማለች። ሸክሙን በትካሸዋ ላይ ጣል እድርጋ ፈጠን እያለች ስትራመድ ላየ በፊቷ ላይ አንዳች የብርታትና የጽናት መንፈስን ያነባል።

እንደእኔ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው “ሴት ልጅ እንዴት ይህን ያህል ክብደት ተሸክማ ትጓዛለች?” ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማንዱራ ወረዳ ነዋሪዋ ወጣት ማሪማ ግን ሸክሙ እንደ ኩበት ቀሏት ይሁን ጽናቱን ፈጣሪ ሰጥቷት ባላውቅም በደስታ ወደ ፊት መራመዷን ቀጥላለች።

“የኛ ችግር የምንይዘው ሸክም ሳይሆን የጸጥታ ስጋት ነበር” የምትለው ወጣቷ ባለፉት ዓመታት በኛ ላይ የደረሰው አስከፊ ሰቆቃና መከራ ለጠላትም እንዲገጥመው አልመኝም በማለት ትናገራለች።

ባለፉት ዓመታት በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎች ሲከሰት የነበረው ግጭት የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ለሞት፣ ለስደት፣ ለንብረት መውደም እንዲሁም ለተለያዩ ችግሮች ዳርጓቸው መቆየቱ የቅርብ ትውስታ ነው። አካባቢው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚገነባበት፣ ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ የስኳር ፕሮጀክቶችና ሌሎች የኢንዱስትሪ ልማቶች ያሉበትና ለመተግበር የታቀደበት በመሆኑ የውጭ ሃይሎች ግጭት እንዲነሳ እጃቸውን ሊያስገቡ እንደሚፈልጉ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ወጣት ማሪማ ግጭት በተከሰተባቸው በነዚያ አስከፊ ጊዜያት የነበረውን ሁኔታ፣ የደረሰውን ጉዳት፣ በተከፈለው መስዋዕትነት የመጣውን ሰላም በሚያስታውስ የተስፋ ስሜት "ጸረ ሰላም ሃይሎች ያስነሱት ግጭት ለዘመናት በአንድነት የኖረውን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ተስፋ አጨልሞት ነበር፤ በሰላም እጦት ሁሉም ህዝብ ጫካ ገብቶ ኑሮውን ከዱር አውሬ ጋር ያደረገበት የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው" ትላለች።


በአሁኑ ወቅት ጸረ ሰላም ሃይሎችና ተባባሪዎቻቸው የፈጠሩት ሰው ሰራሽ ችግር ሊፈታ መቻሉ እፎይታን መፍጠሩን ትገልጻለች።

በወቅቱ ሕክምና፣ መድሃኒትና ሌሎች የጤና መጠበቂያ ቁሶች ባለመኖራቸው ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በወባ እና ሌሎች በሽታዎች ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች እንዳሉ በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት የጸጥታ አካላትና ሰላም ፈላጊ የአካባቢው ተወላጆች ከመንግሰት ጋር በመሆን ባደረጉት ጥረት የነበረው ግጭት ተወግዶ በአካባቢው ሰላም ሰፍኗል። ይህም ለማሪማና ለአካባቢው ነዋሪዎች እፎይታን በማጎናጸፉ በጣም ደስተኛ ናቸው። የተገኘውን ሰላም ተከትሎ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማንዱራ ወረዳ ተነስታ በአማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ ከተማ በመምጣት ለመገበያየት በቅታለች። ከጓደኞቿ ጋር ከቻግኒ ከተማ የሚፈልጉትን ገዝተው ወደ አካባቢያቸው ወስደው በትርፍ ለመሸጥ ምቹ ሁኔታም ተፈጥሮላቸዋል።

በቻግኒ ከተማ የቅዳሜ ገበያ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ። በርበሬ፣ የተለያዩ የጥራጥሬ፣ የቅባትና የአገዳ ምርቶች ለሽያጭ ይቀርባሉ። አልባሳት፣ የሴቶች ጌጣጌጥ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች እንዲሁም ሌሎች የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ንግድ ልወውጥ የሚካሄድባት ከተማ መሆኗን በነበረኝ የአጭር ጊዜ ቆይታ አስተውያለሁ።

ገበያተኛው የተፈጠረውን ሰላም በማጣጣም ላይ መሆኑን በገበያው ውስጥ ከሚያሳየው መስተጋብር መረዳት ቀላል ነው። እኔም ይሄን በተደጋጋሚ ታዝቢያለሁ። ከህዝቡ ፊት ያነበብኩት በግጭቱ የተነሳ በደረሰው ችግር ምክንያት ቁርሾና ቂም በቀል ውስጥ መግባትን ሳይሆን የሰላምና እርስ በርስ መዋደድና የመደጋገፍ ስሜትን ነው። ይሄን ደግሞ በቻግኒ ከተማ በሚካሄደው የቅዳሜ ገበያ መስተጋብር ላይ ተገኝቶ ማረጋገጥ ይቻላል። ገበያው የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች ያላቸውን ይዘው መጥተው በነጻነት የሚገበያዩበት ነው። አሁን በሰላም ተገበያይቶ ወደ ቤት የሚመለስበት ሁኔታ በመፈጠሩ ለወጣት ማሪማ እና እንደ እሷ ላሉ ወጣቶች ደስታና እፎይታን ሰጥቷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የማንዱራ ሚሊሻ የሆኑት አንመይ አልቤም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም መታጣት ችግር ዛሬ መፈታት በመቻሉ በነጻነት ያለስጋት ለመገበያየት መብቃቱን አስረድቷል። "ያ አሰቃቂና የእልቂት ጊዜ አልፎ ተገናኝተንና እርስ በርስ ተገበያይተን በሰላም ወደየቤታችን እንመለሳለን ብሎ ማሰብ እንደ ከንቱ ህልም ነበር" ይላል የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ።

“ሚሊሻ እንደመሆኔ ከፌዴራልና ከክልሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ግጭት ቀስቃሾችን ለመፋለም ጨካ ለጫካ ያሳለፍነው ጊዜ መቼም አይረሳኝም” ያለው ሚሊሻ አንመይ፣ ስንቶች በሕክምና፣ በመድሃኒትና ምግብ እጦት ህይወታቸው ማለፉን አንስቷል። "አማሟቴን አሳምረው" እንደሚባላው በወጉ መሞትና መቅበር ትልቅ ጸጋ መሆኑን የገለጸው አንዳች የሀዘን ስሜት ውስጥ በመግባት ነው።

አሁን ላይ ሁሉም የደረሰውን ጉዳት በመርሳት የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተንቀሳቀሰ ነው። የሁለቱ ክልል ህዝቦች ቂም በቀልን ትተን በጋራ የምንሰራበት ወቅት ላይ መድረሳችን ህዝቡ ከጥንት ጀምሮ ያለው የመተሳሰብ፣ የአብሮነትና አንድነት የመንፈሰ ጠንካራነት ማሳያ እንደሆነም ነው የገለጸው።

በእርግጥም የማንዱራ ሚሊሻው እንዳለው በአካባቢያቸው ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው ህጻናት ያለስጋት በመማር ላይ ናቸው። የጤና ተቋማትም የተለመደውን የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ነው። በሰላም እጦት ተዘግተው የነበሩ መንገዶች በመከፈታቸውም ሁሉም ተሯሩጦ ኑሮውን ለማሸነፍ ላይ ታች እያለ ነው። ባለሃብቶችም በክረምቱ በግብርናው መስክ ተሰማርተው ማልማት ችለዋል። የጸጥታ ስጋት ተወግዶ ሌሎች የልማት ሥራዎች ሲተገበሩ ማየት ትልቅ ስኬት ነው።

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የቻግኒ ከተማ ነዋሪ አቶ ሲራጅ አዲስ እንዳሉት ግጭት በነበረበት ወቅት በአካባቢው የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ ተዳክሞ ነበር። እሱ ቀርቶ በሰላም ውሎ ለማደር ጊዜው ከባድ ነበር ይላሉ።

"የተገኘው ሰላም በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በህብረተሰቡ የጋራ ጥረት በመሆኑ ሰላሙ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል" ብለዋል። አሁን ላይ ያለፈውን የመከራ ጊዜ፣ በሞት የተለየውን ወገን፣ የወደመውን ሀብትና ንብረት በመርሳት በተገኘው ሰላም በጋራ ሰርቶ ራስንና አካባቢውን ለመለወጥ መትጋት እንደሚገባ ነው የመከሩት። ያለፈን በደልና ቅሬታ በእርቅና በይቅርታ በማለፍ ነገን ብሩህ ለማድረግ መትጋት አለብን በማለትም ነው ያስገነዘቡት።

አቶ ሲራጅ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የጉሙዝ ማህበረሰብ ወደ ቻግኒ መጥቶ ያለውን ሽጦ የሚፈልገውንም ገዝቶ ይሄዳል፤ እነሱም ወደ መተከልና ማንዱራ በመሄድ ያላቸውን ይሸጣሉ፤ የፈለጉትንም ገዝተው የሚመጡበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይሄን አብሮነት በማጠናከር ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን ማጽናት ላይ ጠንክሮ መስራት ይገባል።

በአማራም ሆነ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ወንጀለኞችን አጋልጦ ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋል። አሁንም የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን አደብ እንዲገዙ ማድረግ ተገቢ ነው። ወንጀለኛን ለህግ አጋልጦ መስጠትን ከተለማመድን ነገም አካባቢውን የጦር ቀጣና ለማድረግ የሚፈልጉ የጥፋት ሃይሎች መግቢያ ቀደዳ አይኖራቸውም ይላሉ።

ሃገር በአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዜጎች የተባበረ ክንድ ትገነባለች፤ ደህንነቷም ድንበሯም ይጠበቃል። ለዛሬው ትውልድ የደረሰችውም የብዙዎች ዋጋ ተከፍሎባት እንደመሆኑ በጋራ በሰላምና በአብሮነት ይሄንኑ ማስቀጠል የግድ ይላል። በተለይም የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት የሚወስድ እንደመሆኑ አካበቢን የመጠበቅ የነቃ ተሳትፎን ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ልታለማውና ልትጠቀምበት የምትችለው ገና ብዙ ያልሰራችበት ሃብት ባለቤት መሆኗ የአንዳንድ ሃይሎችን ቀልብ መሳቡ የሚጠበቅ ነው። ሰላሟ ሲረጋገጥ የዜጎች ደህንነት ሲከበር የተጀመረው የእድገት ጉዞ መፋጠኑ የማይቀር በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም