የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እየተነቃቃ የመጣውን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል- የሆቴል አሰተዳደሮች

46

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 26/2015 በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እየተነቃቃ የመጣው የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆቴል አስተዳደሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝና በሰላም ችግር ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ኮንፍረንስ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መነቃቃቱ ይታወቃል፡፡

ይህንን የበለጠ ለማጎልበት የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የሚመጡ እንግዶች በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና በመልካም መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

የዘሞዛይክ ሆቴል ኦፕሬሽን ማኔጀር ወይዘሪት ምዕራፍ ቀለሙ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የሆቴሎች እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ባለፈው የገና በዓል በርካታ ቱሪስቶች መጥተው ተስተናግደዋል።

በተለይ ባለፉት አምስት ወራት በሆቴል ዘርፍ ላይ እየታየ ያለው መነቃቃት ጥሩ በመሆኑ ፕሮግራማቸውን ሰርዘው የነበሩ ጎብኝዎች እንደገና የመምጣት ጥያቄዎች እያቀረቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ መነቃቃት እያሳየ ላለው የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ ተስፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንግዶችንም ለመቀበል ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ከሀበሻ ልብስ ጀምሮ የተለያዩ የቡና ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ በማቅረብ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የካሌብ ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታብቻ ደጀኔ፤ በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣውን የቱሪዝም ኮንፍረንስ በማሳደግ ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

ለእንግዶች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠትና በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አሻራ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አስቴር ሰለሞን በበኩላቸው የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እየተነቃቃ መምጣቱን ጠቅሰው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ይህንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴሎች እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ትላልቅ ዝግጅቶችን በማስተናገድ የታወቁ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዘዳንቷ ይህንን ልምዳቸውን በዘንድሮው የሕብረቱ ጉባኤ ላይ ለመድገም ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ማንኛውም እንግዳ ከአይሮፕላን ወርዶ ቀጥታ የሚሄደው ወደ ሆቴል መሆኑን በማሰብ የመጀመሪያ የአገር ገጽታለመገንባት መዘጋጀት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም