በአማራ ክልል በበጋ ወራት ከ232 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ነው

33

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 26/2015 በአማራ ክልል በበጋ ወራት የመስኖ ስንዴን ጨምሮ ከ232 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ያለውን የገፀና ከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም የበጋ መስኖ ልማት እየተከናወነ ነው።

በዘንድሮው የበጋ ወራት 257 ሺህ 755 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ እስካሁን በተደረገ ጥረት 232 ሺህ 742 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።

በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው መሬት 207 ሺህ 195 ሄክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን ጠቁመው፤ ቀሪው በአትክልት፣ ስራስር፣ ቅመማቅመም፣ ጥራጥሬና ቋሚ ተክሎች የለማ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ይበልጣል እንዳሉት ለበጋ መስኖ ልማቱ 294 ሺህ 208 ኩንታል ምርጥ ዘርና 263 ሺህ 949 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል።

በዚሁ የበጋ መስኖ ልማት ከ900 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በዘንድሮ የበጋ ወራት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር መስኖ ከ45 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ እና ቀይ ስር እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ አርሶ አደር ሃብታሙ አበራ ናቸው።

የቢራ ገብስ በመስኖ ማምረት ከጀመሩ 15 ዓመት እንደሆናቸው ጠቁመው፣ ምርቱን ለዳሽን ብቅል ፋብሪካ በማስረከብ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮ የበጋ ወቅት በኩታ ገጠም እርሻ በመስኖ እያለሙት ካለው ስንዴና የቢራ ገብስ የተሻለ ምርት በማምረት 150 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"መንግስት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት በያዘው ዕቅድ መሰረት በመበረታታት ባለኝ አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ስንዴ እያለማሁ ነው" ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር ሞላ ይሁን ናቸው።

ያለሙት የበጋ መስኖ ስንዴ በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ከ70 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው 239 ሺህ ሄክታር መሬት 41 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም