የሆስፒታሉ የመልሶ ማቋቋም ሥራ የአገልግሎት አሰጣጡ ጥራቱን አሻሽሎታል - ተገልጋዮች

151

ሰቆጣ ( ኢዜአ) ጥር 26 ቀን 2015 የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተደረገለት የመልሶ ማቋቋም ሥራ የአገልግሎት አሰጣጡ ጥራቱን ማሻሻሉን የሆስፒታል ተገልጋዮች አስታወቁ።

በሆስፒታሉ የድህረ ወሊድ አገልግሎት ሲጠቀሙ ኢዜአ ያገኛቸው ወይዘሮ ፀጋ ፍቃዱ እንደገለፁት፤ በሆስፒታሉ ባለሙያዎች በተደረገላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ልጃቸውን በሰላም እንዲገላገሉ አስችሏቸዋል።

ካሁን ቀደም ሆስፒታሉ በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ጦርነት የህክምና መሳሪያዎች ጎድለው ስለነበረ በትንሽ ህመም ሁሉ ሪፈር ወደ ሰቆጣ ይላኩ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የጎደሉ የህክምና መሳሪያዎች መሟላት በመጀመራቸው የአገልግሎት አሰጣጡ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በቀጣይም የህክምና መሳሪያዎችን ይበልጥ በማሟላት በሪፈር ሰቆጣና ባህር ዳር የሚላከውን ታካሚ ድካምና እንግልት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ሊሠራ እንደሚገባ ወይዘሮ ፀጋ ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ የመጀመሪያ ልጃቸውን ተገላግለው ያገኘናቸው ወይዘሮ ታምር አያሌው በበኩላቸው፤ ለወሊድ ከገቡበት ቀን ጀምሮ በህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

'' በሆስፒታሉ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትም ወላድ እናቶች በጤና ተቋም መጥተው እንዲወልዱ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

አቶ አወቀ መኮነን በሰጡት አስተያየት፤ የልብ ህመም ታመው ለመታከም ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ወዲህ የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ መኖሩን መታዘባቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በሆስፒታሉ የልብ መመርመሪያ መሳሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈር መላካቸውን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት የታካሚውን እንግልትና ወጭ ሊቀንስ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ካሰች ማሞ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም በመንግስትና በረጅ ድርጅቶች በተደረገለት የመልሶ ማቋቋም ሥራ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ተችሏል።

ካሁን ቀደም በሆስፒታሉ የራጅና መሰል ማሽኖች በጦርነቱ ለውድመት በመዳረጋቸው በመሳሪያ እጥረት ምክንያት ብቻ ህሙማን ወደ ሰቆጣ ይላኩ እንደነበርም ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ በተደረገለት የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከእናቶችና ህፃናት ህክምና በተጨማሪ በሌሎችም የህክምና አገልግሎቱ አሰጣጡ ላይ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የልብ መመርመሪያ መሳሪያ በሆስፒታሉ ደረጃ ምክንያት በዚህ የሚሟላ ባለመሆኑ ህሙማን ወደ ፈለገ ህይወት ሪፈር ይላካሉ ብለዋል።

የአምደወርቅ የመጀመሪያ ሆስፒታል ስድስት ጤና ጣቢያዎችን የሚያስተሳስር ሲሆን፤ በዓመት ከ140 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም