ማዕከሉ በጦርነት ከደረሰበት ውድመት አገግሞ ከ270 ሺህ በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን እያባዛ ነው

55

ደሴ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል በጦርነቱ ከደረሰበት ውድመት መልሶ በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ270 ሺህ በላይ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን እያባዛ መሆኑን አስታወቀ።

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐሰን እንድሪስ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ፣ በሽታን የሚቋቋሙና የተሻለ ምርት የሚሰጡ ችግኞችን በማባዛት እያቀረበ ይገኛል።

ማዕከሉ በዓመት 2 ሚሊዮን ችግኝ የማባዛት አቅም ላይ ደርሶ እንደነበር ጠቅሰው፣ በጦርነቱ በደረሰበት ውድመት አቅሙ መቀነሱን ገልፀዋል።

ይሁንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ጥረት ማዕከሉን መልሶ በማቋቋም ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን አቶ ሐሰን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመጪው ክረምት የሚተከሉ ከ270 ሺህ በላይ የሙዝ፣ የአናናስ፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የድንች እና እንሰት ችግኞችን የማባዛት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

"ችግኞቹ የአካባቢውን አየር ፀባይ የሚላመዱ ሲሆኑ እስከ መጪው ሐምሌ ወር ድረስ ለአርሶ አደሮችና ለባለሀብቶች ይሰራጫሉ" ብለዋል።

የማዕከሉን አቅም የበለጠ ለማጠናከርም ከአማራ መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽህፈት ቤት በተገኘ የ17 ሚሊዮን ብር በጀት ድጋፍ የተጎዱ መሳሪያዎችንና ሼዶችን የመጠገንና የማጠናከር ስራም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በማዕከሉ የምርትና ብዜት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ በላይ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ከማዕከሉ የተሰራጩ ችግኞች በምርታማነታቸው፣በሽታን የመቋቋም አቅማቸውና በፍጥነት ምርት በመስጠት ተመራጭ ያደርጋቸዋል።

"አርሶ አደሩና ባለሃብቱ የችግኞችን ውጤት በተግባር በማየታቸው ፍላጎታቸው እያደገ ነው" ብለዋል።

"በማዕከሉ መልሶ የማቋቋም ሥራ ቤተ-ሙከራዎችን፣ መቆጣጠሪያ ክፍሉን፣ የውሃ ማጣሪያ ማሽኖችና ሌሎችንም በመጠገን ሌት ተቀን ለመስራት ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

"አካባቢያችን ለቆላ ፍራፍሬ ምቹ ቢሆንም ነባሩ ዝርያ በበሽታና ምርት ለመስጠት በሚወስደው ረጅም ጊዜ በድካማችን ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ነበር" ያሉት ደግሞ አቶ ኢብራሂም ሸህ ሙሄ ናቸው።

ከቲሹ ካልቸር ማዕከል ወስደው በ2013 ዓ.ም የተከሉት ሙዝ በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ለምርት ከመድረሱ ባለፈ በምርታማነቱ የተሻለ መሆኑን በተግባር በማየታቸው ዘንድሮ ሌሎች ችግኞችን ተረክበው ለማባዛት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ሥራውን በ2011 ዓ.ም መጨረሻ የጀመረ ሲሆን በሂደት በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ችግኝ የማባዛት አቅም እንደሚገነባ ከማዕከሉ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም