ቀጥታ፡

የናይል የትብብር መድረክ የተፋሰሱን ሀገራት አንድነት ለመፍጠር አስችሏል- አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ

አዲስ አበባ መስከረም 25/2011 የናይል የትብብር መድረክ የተፋሰሱን ሀገራት አንድነት በመፍጠር በተፋሰሱ ላይ የጋራ የልማት መርሃ ግብር ቀርጸው እንዲሰሩ ማስቻሉን የምስራቅ ናይል ቴክኒክ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የተፋሰሱ ሀገራት ህጋዊና ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የአባይን ተፋሰስ በጋራ ለመጠቀም እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ 1997 ጀምሮ ለ13 ዓመታት ድርድር አድርገዋል። ድርድሩ ከተደረገ በኋላ በናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ይዘት በወቅቱ የነበሩ ዘጠኙ ሀገሮች ተስማምተዋል፤ ምንም እንኳን ግብጽ፣ ሱዳንና ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ባይፈርሙም። ደቡብ ሱዳን በወቅት ሉዓላዊት አገር ስላልነበረች እንዲሁም ኤርትራ ራሷን ስላገለለች ባይሳተፉም፤ በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ተቀብላ ለማጽደቅ እንቅስቃሴ ጀምራለች። የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተፋሰሱ ሀገራት በቴክኒክ ትብብር አማካኝነት የልማት ፕሮጀክቶችን መገንባት ጀምረዋል። የቴክኒክ ትብብሩ ህጋዊና ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ሊደርስበት የሚችለውን ፖለቲካዊ እንቅፋት ለመፍታት ሁነኛ አማራጭ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም የተፋሰሱ አገራት በመረጃ አሰባሰብ፣ በአቅም ግንባታ፣ በመተማመን፣ በፖሊሲዎችና አደረጃጀቶች፣ መርሃ ግብሮችን በመቅረጽና በመተግበር የትብብርን ጥቅም እንዲያውቁ ያደርጋል ብለዋል። የናይል ተፋሰስ ዓለም አቀፍ የውሃ ህግን በተከተለ መንገድ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የሚደረገው ሂደት የዘገየ ቢሆንም በ1999 የቴክኒክ ትብብሩ ከተጀመረ በኋላ የተፋሰሱ ሀገራት የተስማሙባቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል። ጣና በለስና ርብ ግድብ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በናይል ተፋሰስ ስር የሚካተቱ በተፋሰሱ ሀገሮች አውቀውና ተስማምተው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም አውስተዋል አቶ ፈቂአሕመድ። የተፋሰሱ ሀገራት በናይል ወንዝ ላይ ተሰባስበው በመመካከር የጀመሩት የልማት ፕሮጀክት ለቀጣናው ሰላምና ልማት የጎላ ሚና እንዳለው የገለጹት አቶ ፈቅአሕመድ፤ በቴክኒክ ሂደቱ የማትሳተፈው ግብጽም ቢትሆን የምትጎዳው ራሷን መሆኗን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የተፋሰስ እንክብካቤ ፕሮጀክት እንዲሁም የኢትዮጵያና የሱዳን የሃይል ግንኙነት የተቀረጸው በምስራቅ ናይል የተቀናጀ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። በወቅቱ በድርድሩ ላይ ሉዓላዊት ሀገር ያልነበረችው ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ለማጽደቅ እንቅስቃሴ መጀመሯን የገለጹት አቶ ፈቂአሐመድ፤ ሌሎች ሀገራትም እንዲያጸድቁት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ቢሆንም ሁሉም አለማጽደቃቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ስምምነቱን ተቀብለው ያጸደቁ ሲሆን ኬንያ፣ ዩጋንዳና ቡሩንዲ በሂደት ላይ ናቸው፤ ስምምነቱን ሁለት ሶስተኛ አገሮች በፓርላማቸው ካጸደቁት የሚፈረምም ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም