የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የንግድና የሎጀስቲክስ ስርዓታችንን እና ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማችንን የሚያሳድግ ነው- የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

138

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የንግድና የሎጀስቲክስ ስርዓታችንን እና ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።  

የገንዘብ ሚኒስትሩ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ድሬዳዋን ከወደቦች ጋር የማስተሳሰር ስራዎች በቀጣይነት ይሰራል። 

የደረቅ ወደብና ተርሚናል መገንባት በቀጣይ ለሚከናወኑ የሎጀስቲክስ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል። 

በድሬዳዋ የተገነባውን የደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታ ዓይነት ትልቅ መሰረተ ልማት ማካሄድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል። 

የደረቅ ወደብና ተርሚናል መሰረተ ልማት ግንባታዎች የንግድና የሎጀስቲክስ ስርዓታችንን እና ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማችንን የሚያሳድግ ነው ብለዋል። 

የዛሬውን ደረቅ ወደብና ተርሚናል ጨምሮ በድሬዳዋ የተገነቡት እና አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ነፃ የንግድ ቀጠና፣ የዘመናዊ ባቡር እና የኮንክሪት አስፋልት መንገዶች አገራችንን ከምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት አገራት ጋር በማስተሳሰር የወጭ እና ገቢ፣ የሎጀስቲክ አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል ሚኒስትሩ። 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ደነጌ ቦሩ በበኩላቸው ለደረቅ ወደብ ግንባታ በተሰጠው ትኩረት እስካሁን ስምንት ደረቅ ወደቦች ተገንብተው ወደ ስራ በመግባታቸው በዓመት በአማካኝ 597 ሺህ ኮንቴነር የማስተናገድ አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል። 

ይህም የሎጀስቲክስ ስርዓት ተግዳሮት የሆኑትን ጊዜና ወጪን በመቀነስ የሎጀስቲክ ስርዓትን ለማዘመን እያገዘ እንደሆነ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልገሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናሉ ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱን ገልጸዋል። 

በውስጡ የተገነቡት ዘመናዊ ተቋማት በዘርፉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በአመት እስከ 128 ሺህ ኮንቴይነር እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል። 

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ደረቅ ወደብ እና ተርሚናል የአገር እና የድሬደዋን ከፍታ ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል። 

የመሰረተ ልማቱ መገንባት የድሬዳዋን የልማት ኮሪደርነት ደረጃ የሚያሳድግ እና ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንደሚጨምር ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። 

ደረቅ ወደቡና ተርሚናሉ በ21 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ባለ ሶስት ወለል የቢሮ ህንፃ፣ መጋዘን፣ የኮንቴይነር ተርሚናልና 10 ሄክታር የውስጥ ለውስጥ የኮንክሪት መንገድ፣ በአንድ ጊዜ 140 መኪናዎች ማቆም የሚችል መሰረተ ልማት ተሟልቶለት የተገነባ እንደሆነ ተነግሯል። 

ሁለት የዕቃ ማስቀመጫ መጋዘን፣ ደረቅ ወደቡን ከኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ጋር የሚያገናኝ 835 ሜትር የባቡር ሃዲድ የተሰራለት መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም