በኢትዮጵያ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነት በእርቅና ይቅርታ መፍትሔ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ዝግጅት ተጀመረ

93

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015  በኢትዮጵያ የተከሰቱ በደሎችን፣ ቁርሾና ኢ-ፍትሕዊነትን በተጠያቂነት መርህ በእርቅና ይቅርታ መፍትሔ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ የዝግጅት ሂደት መጀመሩን ተገለጸ።

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድን ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የባለሙያዎች ስብስብ ሲሆን አባላቱ የፖሊሲ ሰነድ ዝግጅት ሂደቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የባለሙያዎች ቡድን አባል ዶክተር ማርሸት ታደሰ፤ በፖለቲካና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ለማድረግ የሞከሩ አገራት የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትህ ስርዓትን መዘርጋቱ ሲደርሱ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ በደሎችና ቁርሾዎችን በእውነት፣ በፍትሕና በእርቅ በመሻገር ዘላቂ ሰላምና ፍትህ ለማስገኘት ከፍተኛ አስተዋፅዎ እንዳለው ተናግረዋል።

ምህረት መስጠትን፣ የህግና ተቋማት ማሻሻያ ማድረግን፣ ማካካሻ መስጠትን፣ እውነት ማፈላለግን እና ተጠያቂነትን ማስፈንም የሽግግር ፍትሕ ሰነዱ ዓላማ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሰነዱም ዓላማዎቹን በማገናዘብ ሁሉን አቀፍ መፍትሔ እንዲሰጥ ተደርጎ የሽግግር ፍትሕ የደረሰበትን ደረጃ ባገናዘበ መልኩ የዝግጅት ሂደቱ መጀመሩን አብራርተዋል።

አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ የነበረች አገር የደረሰባትን ቁስል፣ በደልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሽግግር ፍትህ እንድትፈታም ነባራዊ ሁኔታዋን መረዳት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ጊዜ የሚጠይቅ ሂደት መሆኑን ጠቁመው ጽንሰ ሃሳቡም የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት እውነት፣ እርቅ ሰላምና ፍትህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተዋል።

በሰነዱም ኢትዮጵያዊያን ሊፈቱላቸው የሚፈልጓቸው ጉዳዮች እንዲካተቱ ለማድረግ ውይይትና ምክክር ይደረግበታል ብለዋል።

ሌላኛው የባለሙያዎች ቡድን አባል አቶ አዲስ ጌትነት፤ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች የነበሩ ማህበራዊ ትስስሮች በመሸርሸር የአገርን ህልውና ሲፈታተኑ እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

በዚህ መነሻነትም ሰነዱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ችግሮችን በሽግግር ፍትሕ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ሰላምን በማረጋገጥ፤ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የማህበረሰብን ትስስር መመለስ ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ የሰነዱ ዋነኛ ዓላማ ይሆናልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም