የለውጡ መንግሥት በፈተና ውስጥም ሆኖ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጡ ልማቶች እየሰራ ነው-ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግሥት በፈተና ውስጥም ሆኖ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጡ ልማቶች እየሰራ ነው-ዶክተር አለሙ ስሜ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 25/2015 ''የለውጡ መንግስት በፈተና ውስጥም ሆኖ የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ልማት በማከናወን የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጡ ስራዎች እየሰራ ነው'' ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለፁ።
''ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልፅግና ጉዟችን ስኬት'' በሚል መሪ ሃሳብ ከባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሄዷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ በመድረኩ እንዳሉት ባለፉት 27 ዓመታት በተሰሩ መልካም ያልሆኑ ስራዎች የኢትዮጵያን እድገት የሚጎዱ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዚህም የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ሃብት ፈሶ የማይጠናቀቁበት፣ የኢትዮጵያ በከባድ እዳ ውስጥ መዘፈቅ፣ ተቋማት በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት መቃኘትና መሰል ችግሮች እንደነበሩ ገልፀዋል።
ከችግሩ መክፋት የተነሳም ከውስጥና ከውጭ በመጣ ግፊት ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው፤ የለውጡ መንግስት ችግሩን ለመቀልበስ ሰፊ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
በተለይም ሀገራዊ ፓርቲ በመመስረት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ የመከላከያ፣ የፖሊስና የደህንነት ተቋማት ነፃነታቸው ተጠብቆ እንዲደራጁ በማድረግና መሰል ተግባራትን በተለያዩ ችግር ውስጥ ተሁኖም ሊከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግሥት በፈተናዎች ውስጥ ጭምር ሆኖ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና የጎርጎራና መሰል አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የኢትዮጵያ ህዳሴና ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጡ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
እንዲሁም ሃገሪቱ በምግብ እራሷን እንድትችል ከማድረግ አልፎ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ድህነትን በዘላቂነት ማስወገድና ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አሁን የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና የሃገሪቱ እድገት እንዲረጋገጥ ተባብሮና ተጋግዞ መስራት እንደሚገባ ዶክተር አለሙ አስገንዝበዋል።
ለሃገርና ህዝብ ደንታ የሌላቸውና በግል ጥቅም የታወሩ አካላት የሚፈጥሯቸውን አጀንዳዎች ወደ ጎን በማለት የኢትዮጵያን አሁናዊ ፈተና መረዳት፣ ከፈተና የምትወጣበትን መንገድ መደገፍና አንድነታችን የሚፈታተኑ ጉዳዮችን በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ችግሮችን ተሻግሮ የመጣው ለውጥ በፖለቲካ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና በማዕድን ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግስት በፅንፈኛ ቡድኖች የገጠመውን ጦርነት በመቋቋም በሁሉም ዘርፍ ዘላቂ ለውጥ በማምጣት ኢትዮጵያን የማፅናትና ሉአላዊነቷን የማስከበር ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በተለይም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ አንድነቷን በማፅናት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነቷ እንዲጎላ በማድረጉ ለዘላቂ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።
ፅንፈኝነትን ለማምከን አንድነትን በማጠንከር ችግሮችን በውይይት፣ በመመካከር፣ በትዕግስትና በፅናት መፍታት እንደሚገባ ርዕሰ-መሰተዳድሩ አመልክተዋል።

''ለሃገራችን ዘላቂ ደህንነት ከቸልተኝነትና ምን አገባኝ ከማለት ተላቀን በጋራ ዘብ ልንቆም ይገባል'' ያሉት የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ተስፋሁን ታደገ፤ ጠብ ከሚያጭሩና ጥላቻን ከሚዘሩ ተጨባጭ ካልሆኑ መረጃዎች እራስን በመቆጠብ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መነጋገር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ሌላው የውይይቱ ታሳታፊ አቶ ይስማው ልመንህ መንግስት የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀልን፣ የፀጥታ ችግርንና ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ፈጥኖ ሊፈታ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ በየደረጃው ካሉ አመራሮች በተጨማሪ የባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።