የባህርዳር ከተማን ከጣና ሃይቅና ከጢስ አባይ ፏፏቴ ጋር አስተሳስሮ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ባህርዳር (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የባህርዳር ከተማን ከጣና ሃይቅና ከጢስ አቧይ ፏፏቴ ጋር አስተሳስሮ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

"ጥርን በባህርዳር" የተሰኘ የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያለመ መርሃ-ግብር አካል የሆነው የባህል አውደ-ርዕይ በከተማዋ ተከፍቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው በአውደ ርዕይው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ከተማዋ በተለያዩ መስህቦች የታደለች በመሆኗ ያለውን ሃብት በአግባቡ ማልማትና ማስተዋወቅ ይገባል።

ዛሬ የተከፈተው አውደ-ርዕይ ዋና ዓላማም የባህል አልባሳት፣ የባህል ምግብና መጠጥ፣ የዕደ ጥበብና ሌሎች ምርቶችን በማስተዋወቅ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአውደ ርዕይው የሚሳተፉ በንግድና በጥበብ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦችን ትስስር በማጠናከር ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

"ትልቅና የሚያምር የባህል አልባሳት እያለን የውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆነናል'' ያሉት አቶ ጋሻው በአውደ ርዕይው የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች የባህል ምርቶችን ገዝተው እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የከተማዋ ህብረተሰብም በአውደ ርዕይው የሚገኙ ባህላዊ አልባሳትና ሌሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

ይህም ከተማዋ ከምትታወቅባቸው የጣና ሃይቅ፣ የአባይ ወንዝና የጢስ አባይ ፏፏቴ ባሻገር የባህል አልባሳትና ሌሎች ምርቶችን በማስተዋወቅ በዘላቂነት የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአውደ ርዕይው ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል 'ጥሩዬ የባህል አልባሳትና የስጦታ ዕቃዎች' ባለቤት ወይዘሮ ጥሩዬ ካሳ በሰጡት አስተያየት አውደ-ርዕዩ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ገቢያችን ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት።

''አሁን ላይ ሀብረተሰቡ ወደ ራሱ ባህል እየመጣ በመሆኑ እኛም የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን በአውደ ርዕይው ይዘን በመቅረብና በመሸጥ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራን ነው'' ብለዋል።

እስካሁን በሚካሄዱ አውደ ርዕይዎች በመሳተፍም የባህል አልባሳትና የስጦታ ዕቃዎችን ውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያን በመላክ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

"የባህል በአውደ ርዕይ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዳስተዋውቅ ዕድል ሰጥቶኛል'' ያሉት ደግሞ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ዘርፍ የተሰማራው ወጣት ሰሎሞን መንግስቴ ነው።

በቀጣይ ምርቶቻችንን ይበልጥ በማስተዋወቅ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን በየጊዜው መሰል አውደ ርዕይዎች በመንግስት በኩል ቢዘጋጁ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህል አውደ ርዕይውም የተለያዩ የባህል አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የባህል ምግብና መጠጦች፣ የባህርዳርን ገፅታ የሚያሳዩ ፎቶዎችና ሌሎች ምርቶች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም