የኑሮ ውድነት ችግርን የማቃለል ተግባር በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

182

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የዜጎች መሰረታዊ ጥያቄ የሆነውን የኑሮ ውድነት ችግር የማቃለል ተግባር በቀጣይም በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። 

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል። 

የምክር ቤቱ አባላት በውይይቱ ላይ በተለይም የኑሮ ውድነት ችግርን በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቷ ማእዘናት በስፋት የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በተመለከተም እንዲሁ። 

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄና አስተያየቶች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ድፍድፍ ዘይት በመቅረቡ ግብዓቱን ተጠቅመው ያመረቱት ከ69 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ለሕብረተሰቡ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል። 

''በስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 67 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ በተለያዩ ምክንያቶች 445 ሺህ 532 ኩንታል መቅረቡን ገልጸዋል።  

ለዚህም ከውጭ በግዥ እንዲገባ የተፈቀደው 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር በዓለም የገበያ ዋጋ መናር ሳቢያ ግዥው መጓተቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። 

መንግሥት መሰረታዊ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በፈቀደው መሰረት 47 ነጥብ 9 ሚሊየን ሊትር ዘይት መግባቱንም ጠቅስዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ሩዝ እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጦችን በማስገባት ዋጋ ለማረጋጋት ጥረት ስለመደረጉ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል። 

የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ሕገ-ወጥ ደላሎች፣ የንግድ ድርጅቶችና ምርት የሚሸሽጉ አካላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።  

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከወጭ ንግድ ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።

'በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ፤ ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን መከላከል እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ ተጨማሪ ስራዎችን በቀጣይ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም