የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር ተቀበለ

41

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተባብሮ መስራትና የፖሊስ ተቋማቱን በትምህርትና ስልጠና ማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን ለመከላከል እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህረት ፕሮግራሞች 38 የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን ለማስተማር መቀበሉ ተጠቅሷል።

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ወደ ኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ዕድል ለመጡ የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዘመናት ከሀገራችን አልፎ የጎረቤት ሀገራት የፖሊስ አመራሮች እና አባሎችን በማስተማር ለቀጠናው ሰላም እና ደህንነት ግንባታ አስተዋጽኦ እያበረከተእንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተባብሮ መስራትና የፖሊስ ተቋማቱን በትምህርትና ስልጠና ማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሶማሊያ አቻቸው ሜጀር ጀነራል አብዲ ሀሰን መሀመድ ጋር በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶማሊያ ወጣት ፖሊስ አመራሮች ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

በስምምነቱም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህረት ፕሮግራሞች 38 የሶማሊያ ፖሊስ መኮንኖችን በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለማስተማር መቀበሉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሶማሊያ ፖሊስ በተጨማሪ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የፖሊስ መኮንኖችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ ገልጸዋል፡፡

ለትምህርት የመጡት የሶማሊያ የፖሊስ መኮንኖች በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፉት አራት አመታት የተከናወኑ ተጨባጭ የሪፎርም ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ከተማሪዎቹ መካከል አስተያያት ሽብርተኝነትና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የፖሊስ ኃይላቸውን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመመከት የሚያስችል ትምህርትና ሥልጠና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እንደሚያገኙ እምነታቸው ገልጸዋል።

ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሁን ላይ እየተጠቀመባቸው ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንደተሞክሮ ወስደው አቅማቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም