የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የካፒታል ገበያ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የካፒታል ገበያ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴን ለመጀመር የሚያስችል አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ወደ ተግባር ለመለወጥ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንና ከኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ጋር በመተባበር ”የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ”ን በማስመልከት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ፤ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴን ለማስጀመር የፀደቀውን አዋጅ ወደ ተግባር ለመቀየር ባለስልጣኑን የማደራጀት ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግስት በካፒታል ገበያ ዙሪያ ያወጣውን አዋጅ መሰረት ያደረጉ ደንቦችና መመሪያዎች የማዘጋጀት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

በመሆኑም በዘርፉ ገበያ መቀላቀል የሚፈልጉ አካላት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ አጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። 

በቀጣይ በካፒታል ገበያ መሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች ባለስልጣኑ የሚያወጣቸውን መመሪያዎችና ደንቦች በመመልከት መስፈርቶቹን ሊመለከቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

ከወዲሁ በካፒታል ገበያው ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠርም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ፤ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴ በተወሰነ መልኩ ቢስተዋልም ህጋዊ ማዕቀፎች የተዘጋጁለትና በተደራጀ መልኩ የሚከናወን እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ 

ይህም ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካፒታል ገበያ ተግባራዊ ከማይደረግባቸው 40 ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓት ቆይቷል ብለዋል፡፡

 የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማጎልበት እና ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ዘርፉ ይዞ የሚመጣው አዎንታዊ እድል ስኬታማ እንዲሆን መንግስት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እና ባለሙያዎችን ማብቃት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሀና ተድላ፤ የካፒታል ገበያ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ብሎም ለባለሀብቶች ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። 

በገበያው መሳተፍ የሚፈልጉ አካላትም ከወዲሁ ያላቸውን እውቀት እና ልምድ ማሳደግ ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል። 

ካፒታል ገበያ ኩባንያዎች የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ለገበያ በማቅረብ ሰዎችም ድርሻ ከገዙ በኋላ ተቋሙ ትርፋማ በሆነ መጠን ያላቸውን ድርሻ መልሰው በመሸጥ ከትርፍ ክፍፍል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም