በተያዘው የበጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው

40

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 በተያዘው የበጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በ100 ከተሞችና በ355 ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ድንጋሞ የተመራው የዘርፉ አመራሮች ቡድን የሞጆ አዳማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ ዛሬ ጎብኝቷል።

ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት ከ730 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት አግኝተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከአምና የተሻገሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በ100 ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች እንዲሁም በ355 ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ እየተከናወኑ ያሉትም ከመንግስት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከብድር ውጭ በዋን ዎሽ ፕሮግራም በተገኘ 12 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ መሆኑን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

በ11 ክልሎችና በሁለት የከተማ መስተዳደሮች ከ6 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከእነዚህ መካከል የሞጆ አዳማ፣ ጎዴ ሶማሌ፣ ብቸና በአማራ ክልልና መቀሌን ያቀፈ ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም እየተከናወነ ያለው ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል።

የጎዴና ብቸና ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው የሞጆ አዳማ ፕሮጀክት በስራ ተቋራጮች ምክንያት ከተያዘለት ጊዜ ሁለት ዓመት ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም የግንባታው አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ ከሚቆፈሩት 13 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መካከል የአራቱ ጉድጓዶች ቁፋሮ መጠናቀቁን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከሞጆ አዳማ እየተከናወነ ያለው የውሃ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የሁለት ጉድጓድ ቁፋሮ በቅርቡ የሚጠናቀቅ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ፕሮጄክቱ በተያዘለት ጊዜ ለአገልግሎት እንዲበቃም 24 ሰዓት ስራው እንዲከናወን ባስቀመጥነው አቅጣጫ እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

በተለይም የኤሌክትሮ ሜካኒካል እቃዎች በፍጥነት ከውጭ እንዲገቡ ፍቃድ ተሰጥቶ በአሁኑ ወቅት ግማሹ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ መስመር እየተዘረጋ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቀሪዎቹ ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ ከሚከናወኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ባሻገር በክልሎችም ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የከተማዋ ህዝብ ብዛት እየጨመረ በመሆኑና ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት የሚታይበት በመሆኑ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የንፁህ መጠጥ ውሃን ችግር ከመፍታት ባለፈ ከተማዋ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ኮንፈረንስ ከተማ በመሆኗ የፋብሪካዎችና የኢንቨስትመንት የውሃ ፍላጎቱን ለማሟላትና ከዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለመ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሳይጀመር ሁለት ዓመታት መቆየቱን የገለጹት ከንቲባው፤ በአሁኑ ወቅት የውሃ መስመር ዝርጋታ ወደ አዳማ መግባቱን ጠቅሰው በአርሶ አደሩ ትብብርና ለፕሮጀክቱ በተሰጠው ትኩረት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ይገኛል ብለዋል።

የአዳማ ወንጂ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አህመድ አብዱል ጀሊል በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሉጎና አባገዳ ሳይት በኩል ውሃውን ወደ ከተማ ለማስገባት የሚያስችል የመስመር ዝርጋታ ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት መጨረሻ በከፊል አገልግሎት እንዲሰጥ ርብርብ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

የፕሮጄክቱ ግንባታ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ ሲሆን በ2016 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም