በሴቶች እና ህጻናት ላይ የመብት ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ ነው-የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ

120

አሶሳ (ኢዜአ) ጥር 25/2015በሴቶች እና ህጻናት ላይ የመብት ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ መሆኑነ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

በዚህም በክልሉ የሴቶች ሰብዓዊ መብቶችን በማስጠበቅ ጥቃት ሲፈጸምም ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።

በክልሉ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች እና ህጻናት የተቀናጀ የጤና፣ የህግ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ውይይት በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰይድ ባበክር በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የሴቶች እና ህጸናትን መብቶች ለማስከበር ግንዛቤ በማስጨበጥ ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በሴቶች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው የተቀናጀ የጤና፣ የህግ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎት በአንድ መስኮት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሶሳ እና ፓዌ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት በአብነት ጠቅሰዋል።

የአገልግሎቱ ዓላማ ተጎጂ ሴቶችን በመደገፍ ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ መሆኑንም የቢሮ ሀላፊው ገልጸዋል።

በሴቶች እና ህጻናት ላይ ጥቃቶችን ከመከላከል ጀምሮ ችግሩ ሲከሰት በአንድ መስኮት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የተጠናከረ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚሻ ሃላፊው አመልክተዋል።

የውይይት ሰነድ ያቀረቡት የክልሉ አቃቢ ህግ እና ሴቶች ፎረም ሰብሳቢ ወይዘሮ እመቤት ኦላና ሴቶች ለትውልድ ቀጣይነት ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

መሠረታዊ መብቶቻቸውን የሚያስከብሩ ተጨባጭ ህጎች ወጥተው መተግበራቸው የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ሴቶች መብቶቻቸውን በማስጠበቅ ረገድ በራሳቸው ጉዳይ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም