በስድስት ወራት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ ሊያስከትል የነበረ የሳይበር ጥቃት ሙከራን ማክሸፍ ተችሏል

118

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኪሣራ ሊያስከትል የነበረ የሳይበር ጥቃት ሙከራ ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ የተቋሙን የግማሽ አመት የሥራ አፈጻጸም በሚመለከት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

የሳይበር ደህንነትና ቁጥጥር በማድረግ ረገድ ተቋሙ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተጋላጭነትን ለመቀነስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በሚሆኑና አጠራጣሪ ሁኔታዎችንና ክስተቶችን መነሻ በማድረግ በተቋማት ላይ ልዩ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት። 

በዚህ ረገድ በግማሽ አመቱ በ27 የመንግስት ተቋማትና በ37 የግል ተቋማት በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ 2 ሺህ 145 የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን አንስተዋል። 

ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 49ኙን ማክሸፍ እንደተቻለ ገልጸው፤ በዚህም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ ሊያስከትል የሚችል ጥቃት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል። 

በሳይበር ወንጀሎች ጥቃት ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል የድረ ገጽ ጥቃት፣ የማልዌር ጥቃት፣ የመሰረተ ልማት ቅኝት፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረተ ልማት ጥቃት፣ የሰርጎ መግባት እና የዳታ እገታ ጥቃት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። 

የሳይበር ወንጀሎች ኢላማ ከሆኑ ተቋማት መካከል የጸጥታና የደህንነት ተቋማት፣ ባንኮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የትምህርት፣ የህክምና ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን ተጠቃሽ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ዘርዝረዋል። 

በተለያዩ ጊዜያት የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ባይቻል እንደ አገር ያስከትል የነበረው ኪሳራ ከፍተኛ እንደነበርም አስረድተዋል። 

በተለይም የግለሰቦችና የተቋማት ወሳኝ መረጃዎች መጥፋትና የመንግስትና የህዝብ ሃብት መጭበርበር ያስከትል ስለነበር ጥቃቱን መከላከል በመቻሉ ሀገርን ከብዙ ጥፋት ታድጓል ብለዋል። 

በሳይበር ወንጀል ተሳትፈው ከተገኙት መካከል የተለያዩ የጥፋት አጀንዳዎችን ለማስፈጸም የተቋቋሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ጭምር ያሉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛልም ተብሏል በመግለጫው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም