11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እይታ - ኢዜአ አማርኛ
11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እይታ
በሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ከረጅም ጊዜ መዘግየት በኋላ ረቡዕ በጀመረው ጉባኤ የሃገሪቱን ቀጣይ መፃኢ ቅርፅ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጀመሩት ፈጣን ለውጥ ጥንካሬን ይሰጠዋል በማለት ግምቱን ያስቀመጠው ሮይተርስ ነው። ሮይተርስ ፅሁፉን ሲቀጥል ጉባኤው በሃገሪቱ የበርካቶች መፈናቀል በቀጠለበት ሁኔታ እንደሚካሄድና ከአንድ ሺ የሚልቁት የጉባኤው ተሳታፊ የግንባሩ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በሊቀመንበርነት ይመርጣሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ አመልክቷል። የምርጫው ውጤትም በታሰበው ሁኔታ ከሄደም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃላፊነት መተማመኛ እንደሚሰጥም ታምኖበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሰዷቸው ፈጣን የለውጥ እርምጃዎች ውስጥ ግንባሩ ዘለግ ላሉ ጊዜያት ሲከተላቸው የነበሩ እምነቶችን ተላልፈዋል ሲል በሃተታው ያነሳው ሮይተርስ፤ ይህም ከዚህ ቀደም በአሸባሪነት ተፈርጀው በውጭ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች እገዳውን በማንሳት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲገቡ አድርገዋል፤ የፖለቲካ እስረኞችንም በነፃ ለቀዋል በሚል በተወሰደው እርምጃና ኢህአዴግ ለዘመናት ጠብቆት በቆየው መርህ መካከል መጣረሶች እንዲኖሩ ሆኗል ሲሉም አንዳንድ ተቺዎችን ዋቢ አድርጎ የዘገባው ፀሃፊ ያነሳል። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ደኢህዴን በአዲስና ወጣት አባሎቻቸው በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤን መታደማቸውን የዘገበው ቢቢሲ የአማርኛው ድረ ገፅ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተጨማሪም የፓርቲዎቻቸውን ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበር፣ የማዕከላዊ እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን አከናውነው ለጉባኤው ዝግጁ መሆናቸውን አመልክቷል። የህወሓት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ቃለ መጠይቅ ያደረገው ድረ ገፁ በተጀመረው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ማን የድርጅቱ ሊቀመንበር ሊሆን ይችላል ብሎ ጠይቋቸው ''አሁን ያሉት ሊቀ መንበር ላለፉት 5 ወይም 6 ወራት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እስካሁን የሠሩት ሥራ ተገምግሞ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል ወይስ አያስፈልገንም የሚለው የጉባኤው ውሳኔ ነው የሚሆነው'' ማለታቸውን አስቀምጧል። በጉባኤው ላይ የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም፣ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምን መልኩ ተግባራቸውን ሊወጡ እንደሚገባ እና በሰላምና መረጋጋት የሚሉ አጀንዳዎች ውይይት እንደሚካሄድባቸውም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። በግንባሩ ጉባኤ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፤ ''የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አፈጻጸም ላይ መቀዛቀዝ ይታያል። ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እሱን እንዴት አድርገን ነው በፍጥነት የምናስቀጥለው የሚለው ትልቁ አጀንዳ ነው። ወደ ሃገር እንዲገቡ የተደረጉ ተፎካካሪ፣ ተቃዋሚ የሚባሉ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ከገቡ በኋላ አንዳንዱ 'አሸንፌ ነው የመጣሁት' ይላል። ሌላኛው 'ወደሽ ሳይሆን ተገደሽ ነው የተቀበልሺኝ' ይላል። ይህ ዓይነት ስሜት የሚፈጥረው የሰላም እና የመረጋጋት ዝብርቅርቅ አለ። ይህን ለመሰሉ ጉዳዮች ጉባኤው ምላሽ ይሰጣል። ይህ የሁላችንም አጀንዳ ነው'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችና ስጋቶች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እርምጃ ሊወስዱባቸው ይገባል። ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ድርጅቶች ተጠናክረው የህብረተሰቡን ማህበራዊ ሃብት እንዲያጎለብቱ የሚያደርጋቸው አሰራርን ሊተገብሩም ዛሬ ነገ ሳይሉ ይጠበቃል ሲል ሃሳቡን ያስቀመጠው ደግሞ ኳርትዝ አፍሪካ ነው። በተጨማሪም አለፍ ሲልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገ መንግስታዊ መሻሻሎችንም ሊያስቡበት ይገባል፤ ይህም በሃገሪቱ ተንሰራፍቶ ለሚገኘው የብሄር ግጭት መቀነስ ሚናው የጎላ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ አዎንታዊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በተጠናከረ መሰረት ላይ መገንባት አሁን በሃገሪቱ እየተከሰቱ የሚገኙ ችግርችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ያስችላልና ሲልም ነው ኳርትዝ አፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮችን በዳሰሰበት ፅሁፉ የገለፀው። የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ እያካሄደው በሚገኘው ጉባኤው ለውጡን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው አሶሺየትድ ፕሬስ ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ከመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድም አንስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ያደረጉትን ንግግር መሰረት አድርጎ ዘገባውን ያወጣው የሮይተርስ የዜና ወኪል ኢትዮጵያ በልፅጋ ለማየት የሚፈልግ ዜጋ ብሄርን ወይም ሃይማኖትን ያማከለ ጥቃት በወገኑ ላይ መፈፀም አይገባውም ማለታቸውን አክሏል። “ከመካከላችን ማንም እስከተጎዳ ድረስ ሁላችንም እንጎዳለን። አንዱ እስከተጠቃ ድረስ ሁላችንም እንጠቃለን…አንዱ እስከሞተ ድረስ ሁላችንም እንሞታለን።” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን የዜና ወኪሉ አፅንኦት ሰጥቶታል። የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤም ከላይ በየአንቀፆቹ ለተነሱ ጉዳዮች ምላሽን የሚሰጥ ሊሆን ይገባዋል። ከምንም በላይ የሃገር ሰላም ይበልጣልና በሃገሪቱ እያሰለሰ የበርካቶችን ህይወት እየቀሰፈ እንዲሁም ብዙዎችን ለመፈናቀል እየዳረገ ለሚገኘው ደዌ ማርከሻውን ማምጣት ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው።