ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 ....በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት  2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም ተቋማት ለመፈጸም በዕቅድ ያስቀመጧቸውን ተግባራት በማከናወን  እየተመዘገበ የሚገኘውን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የ2015 በጀት ዓመት የግማሽ ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና ዘርፎች አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።

በአፈጻጸም ግምገማው ላይም የተቋማት ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርቶችን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሩስያ-ዩክሬን ጦርነት እና በአገር ውስጥ አስቸጋሪ ተጽዕኖዎች ሥር ሆና የተሻለ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ምርት እድገቱም 126 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በማስመዝገብ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት መካከል በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችሏታልም ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የግብርና ሰብል ምርታማነት ለምጣኔ ሃብታዊ እድገቱ መሰረት እንደሆነ ጠቁመው፤ ባለፉት ስድስት ወራትም በአጠቃላይ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በግማሽ ዓመቱም 2 ነጥብ 95 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕቅድ ተይዞ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ መሳብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

የዕቅዱን 65 በመቶ በማሳካት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም 22 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ማሳየት እንደቻለ አንስተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ የሚገኘው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተና ውስጥ ሆናም በሁሉም ግንባር ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ በቀጣይም ከዚህ በላይ ሰፊ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተቋማትም የሕዝብ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል  በዕቅድ ያስቀመጧቸውን ተግባራት ማሳካት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ኢትዮጵያ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት እንደሚገባ ገልጸዋል።

እድገቱንም በተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ እና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄም ተዘግተው የነበሩ 439 ፋብሪካዎች ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት ወደ ሥራ እንዲመለሱ በማድረግ ቀሪዎቹንም ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ተቋማት እያሰመዘገቧቸው የሚገኙ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቀሪ የዕቅድ ሥራዎቻቸውን ለማሳካት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አቅጣጫ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም