ኢትዮ-ቴሌኮም እና የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ክፍያን በቴሌ ብር መሰብሰብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 ኢትዮ-ቴሌኮም እና የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ክፍያን በቴሌ ብር መሰብሰብ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ለገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ ግብርን እና የግል ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ፣ የፌዴራል ታክስ ክፍያን በወቅቱ ለመሰብሰብ እና ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በየጊዜው እያደገ የመጣውን የግብር ከፋዮች የክፍያ አማራጭ ፍላጎት ቀላል እና አስተማማኝ በማድረግ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎች ከግል ወይም ከድርጅት የቴሌ ብር አካውንታቸው በቴሌ ብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም የግብር ክፍያቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ለመክፈል እንደሚያስችል ተነግሯል።

በቴሌ ብር ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ከሚፈጽሟቸው ግብይቶች ከሰበስቡት ገንዘብ ላይ ለግብር ክፍያ በቀጥታ መክፈል የሚችሉበት ሁኔታም ተመቻችቶላቸዋል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም