ቀጥታ፡

ኢጋድ የሰጠንን ሃላፊነት በታላቅ አክብሮት በመቀበል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንሰራለን --የመልካምነት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 25/2015 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ የሰጠንን ሃላፊነት በታላቅ አክብሮት በመቀበል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የኢጋድ የመልካምነት አምባሳደሮች ገለጹ።

የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአየር ንብረት፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሰላምና ደህንነት የጎላ አበርክቶ ለነበራቸው 21 ታዋቂ ግለሰቦች የመልካም አምባሳደርነት ዕውቅና መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ኢጋድ የሰጠን እውቅና ስለ ሰላምና አብሮነት ይበልጥ እንድንሰራ የሚያደርግ ነው ብላለች።

በቀጣይ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እንሰራለን በማለትም ቃል ገብታለች።

በኢጋድ እውቅና የተሰጣቸው ኬንያዊው ሜጀር ጀነራል ጆን ሴይ፤ ላበረከትነው አስተዋጽኦ እውቅና ለሰጠን ኢጋድ እናመሰግናለን ለበለጠ ሃላፊነት እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኢጋድ የቀጣናው ሀገራት በጋራ የሚጠሩበት የወል ስም ሊሆን ይገባል ያሉት ሜጀር ጀነራል ጆን ሴይ፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚሳተፉ አካላት ድል ሲያደርጉ የሄዱበት አገር አሸነፈ ሳይሆን ኢጋድ አሸነፈ ማለት አለባቸው ብለዋል።

ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ በበኩሏ የሰላም ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሰው ልጆች ታላቅ እሴት መሆኑን ገልፃለች።

በመሆኑም ለአፍሪካ ሰላም ወጣቶች ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በንግግር የመፍታት ልምድ እንዲያዳብሩ መልእክቷን አስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም