በኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት እያደጉ መጥተዋል

28

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 በኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት እያደጉ መምጣታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፋይናንስ ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር የባለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት አድርጓል።

የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የባንኩ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ አጠቃላይ በፋይናንስ ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትንና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አብራርተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት በተቀማጭ ሂሳብ፣ በብድር አቅርቦትና ሌሎች ዘርፎች ካከናወናቸው ተግባራት አንጻር ጤናማ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት እድገት እያሳዩ ካሉ ዘርፎች መካከል መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አራት ባንኮችና ሁለት አነስተኛ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን የተሰበሰበ ተቀማጭ ገንዘባቸው 163 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ተናግረዋል።

የሰጡት የብድር መጠንም 63 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሲሆን የተበዳሪዎች ቁጥር ደግሞ ከ39 ሺህ 400 በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ ለመተግበር እየተዘጋጁ ባሉ አዋጅና መመሪያዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ነጥቦችንም ዘርዝረዋል።

ያልተሰበሰበ ብድር (ሊኩዲቲ)፣ የቴክኖሊጂ አጠቃቀም፣ የፋይናንስ አካታችነት፣ የፋይናንስ ደህንነት ከዘረዘሯቸው ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

ባንኮች የሚሰጡት ብድር ለታመለት አላማ መዋሉን ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸውም ምክትል ገዥው አሳስበዋል።

መንግስት ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ ዘርፉን በተጠናከረ መልኩ ለማስጀመር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን የግል ዘርፉም በዚህ አግባብ እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም