የህክምና መሳሪዎችን የአቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንደሚገባ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ

30

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የህክምና መሳሪዎችን የአቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የጤና የሚኒስቴርን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም በመገምገም ውጤታማ ስራዎችን በማድነቅ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም እንዲስተካከሉ አቅጣጫ አስቀምጧል። 

በግምገማው የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትና የህክምና መሳሪዎች የአቅርቦት ችግር መፈታት ይገባል ብሏል። 

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚከሰተውን የወረርሽኝ መስፋፋትና ስርጭት ለመከላከል የቅድመ ዝግጅትና ቁጥጥር ስራም መጠናከር እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ፤ የመድሃኒት እጥረት ችግርን ለማቃለል በተለይም የአገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦትን በማሳደግ ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል። 

የኦክሲጅን አቅርቦት፣ ለእናቶች የመውለጃ አልጋ እጥረትና ሌሎችንም የዘርፉ ችግሮች መፍታት ላይ ሚኒስቴሩ ማተኮር አለበት ሲሉ ተናግረዋል። 

በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል እንዳለበት አሳስበዋል። 

አገሪቱ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ሚኒስቴሩ ለተጎጂዎች ህክምና በመስጠት የሰራው ተግባር የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰው ለባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጥራት ያለው አገልገሎት ለመስጠት ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ሰራዎች መከናወናቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። 

የተለያዩ ችግሮች ውስጥም ሆነን የህዝቡን ጤና ለመጠበቅ፣ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለመስጠትና አቅርቦቶችን ለማሟላት ሰፊ ርብርብ መደረጉን አንስተዋል። 

በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋትና መረጃ በመስጠት ጭምር ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቅሰዋል። 

በቅርቡ በተደረገ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት መከተባቸውን ገልጸው የወባ ወርረሽኝ ለመከላከል ከ10 ሚሊዮን በላይ አጎበር ተሰራጭቷልም ብለዋል። 

የጸረ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለታማሚዎች መድሃኒት በማቅረብ በኩል የተከናወኑ ተግባራትን ጠቅሰዋል። 

የስነ-ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ የነበረው ችግር በመፈታቱ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። 

በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም