ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በመታገል ዘላቂ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ማገዝ ይገባል -ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ

33

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ ) ጥር 24/2015 መንግስት ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በመታገል በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ የጀመራቸው ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ህዝቡ ድጋፉን ሊያጠናክር እንደሚገባ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ አስገነዘቡ።

'ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና አህትማማችነት ለብልጽግና ጉዟችን'' በሚል መሪ ሃሳብ በደብረ ብርሃን ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በወቅቱ እንዳሉት በሃገሪቱ በመጣው ለውጥ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

የለውጡ መንግስት የውጪ ግንኙነትን ለማጠናከርና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን ለማስመዝገብ በሰራቸው ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስርዓት በመዘርጋት በፖለቲካ አመለካከታቸው ከሃገር ተሰደው በውጪ ይኖሩ የነበሩ ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በለውጡ መንግስት የተጀመረው ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ያልተዋጠላቸው ቡድኖች አገሪቱን ለማፍረስ በንጹሀን ላይ ግድያ ሲፈጽሙና ሲያፈናቅሉ መቆየታቸውን አመልክተዋል ።

መንግስት የህዝቦችን የአብሮነት፣ የአንድነትና የሰላም እሴቶችን የሚፃረሩ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በመታገል በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ በመንግስት የተጀመሩ ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ድጋፉን ሊያጠናክር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ህዝቡ ከጽንፈኛና አክራሪ ቡድኖች ጥቃትና ከሃሰተኛ መረጃ ሰጪዎች እራሱንና አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር በበኩላቸው "ጽንፈኝነትና አክራሪነት የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግናን የሚጎትቱ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊታገላቸው ይገባል " ብለዋል።

"በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶች በውስጥ ሀይሎች ብቻ የሚፈፀሙ አለመሆኑን በመገንዘብ ህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያን በመገንባት ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ድርሻ የጎላ ነው" ሲሉም አክለዋል።

መንግስት ጽንፈኝነት ያስከተላቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ትግሉን ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

"የኢትዮጵያን እድገትና ሰላም በማይሹ ቡድኖች የሚሰነዘረውን ጥቃት እየታገልን አካባቢያችንን ማልማት ይገባል" ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ናቸው።

የከተማውን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ900 በላይ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ልማቱ ከአካባቢውና ከክልሉ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ ለባለሀብቶች የሚሰጠውን እገዛና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

ሙሰኞችን ለህግ የማቅረብና ብልሹ አሰራሮችን የማስተካከል ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑም ህዝቡ ድጋፉን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ጽንፈኞች የሚያካሂዱት ጥቃት ማንኛውንም ሀይማኖትና ብሄር የማይወክል በመሆኑ ኢትዮጵያን ለማዳን ተባብረን እንሰራለን" ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ቄስ ዘነበ የሻው ናቸው።

አቶ የሲን መሐመድ በበኩላቸው ጽንፈኛ ቡድኖች የህዝቡን ተከባብሮና ተባብሮ የመኖር እሴት አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉትን ሙከራ ለማክሸፍ በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን በመደገፍ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ከደብረ ብርሃን ከተማ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም