ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ነን-የትምህርት ባለድርሻ አካላት

222

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በደቡብ ክልል የትምህርት ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጥራት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት የትምህርት ጥራት ችግር ሀገራዊ ነው።

ችግሩ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራር አካላት፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ባለፉት ጊዜያት ጀምሮ ተገቢውን ሃላፊነት ባለመውሰዳቸው ያጋጠመ መሆኑንም አስረድተዋል።

ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ ደረጃ ጀምሮ ተገቢውን እውቀት ይዘው ወደ ቀጣይ እርከን እንዲያልፉ ማድረግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥና የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አቶ አንለይ አመላክተዋል።

"በተለይ በቅድመ መደበኛ ደረጃ ተማሪዎች በሰለጠኑና ብቃት ባላቸው መምህራን ተገቢውን ዕውቀት እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል" ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎችም በጉድለታቸው ልክ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት የጥራት ችግርን ለመፍታት ሌላው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ትምህርት የዕውቀት ማግኛና የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚወስን አድርጎ ከማሰብ አንፃር ያሉ ክፍተቶችን መሙላት እንደሚገባም ነው አቶ አንለይ ያመለከቱት።

በእዚህ ረገድ ተማሪዎች ላይ የባህሪይ ለውጥ እንዲያመጡና የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መዘጋጀቱን አረጋግጥዋል።

"በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህሪይ ሳይንስ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር በታ ፃማቶ ናቸው።

"በቅርቡ ይፋ በተደረገው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ብቻ ማለፋቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጠንክረን እንድንሰራ የማንቂያ ደውል ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ለትምህርት ጥራት መውደቅ የተማሪዎች ባህሪይ በራሱ አስተዋጽኦ ስላለው ወላጆች ልጆቻቸውን በቅርበት መከታተልና መደገፍ እንዳለባቸውም ዶክተር በታ ተናግረዋል።

"የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በማሳደግ ትውልድ በመገንባቱ ሂደት የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በእዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጋር አብሮ ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በጋሞ ዞን የጨንቻ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባይነህ ዘለቀ በበኩላቸው፣ "በቅድመ መደበኛ ደረጃ ላይ ተማሪዎች የሚገባቸውን ዕውቀት እንዲቀስሙ አለመደረጉ ለትምህርት ጥራት መጓደል ዋነኛ ምክንያት ነው" ብለዋል።

ከእዚህ በፊት በደቡብ ክልል ከመምህራን እጥረት ጋር በተያያዘ 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች በቂ እውቀት ሳይኖራቸው በመምህርነት ሙያ እንዲቀጠሩ መደረጉ የትምህርት ጥራትን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

በቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት፣ ኩረጃን ማስቀረትና የትምህርት አመራሩ ለሥራው ትኩረት መስጠት በጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት አመራሩ ሚና፣ በሴት ተማሪዎች ተሳትፎና በቅድመ መደበኛ ትምህርት መጠናከር ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም