ቀጥታ፡

የተረጋጋ ዋጋና የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስፈን በቀጣይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል- የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 24/2015 የተረጋጋ ዋጋና የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስፈን በቀጣይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

በመሆኑም የተረጋጋ ዋጋና የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስፈንና ጤናማ የፋይናንስ ስርአት መፍጠር በቀጣይ ትልቁ የብሔራዊ ባንክ ትኩረት እንደሚሆን ነው የገለጹት።

ተግባራዊ የሚደረገው የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ንረቱን እንዳያባብስ በትኩረት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ በተለይም የባንክ ዘርፉ በአገር እድገት ላይ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ያነሱት ዋና ገዥው ባለፉት ስድስት ወራት ከ157 ቢሊዮን ብር በላይ የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛቱን ገልጸዋል።

ይህም የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የፋይናንስ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለው አስተዋጽኦ እየጨመረ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ባንኮች የሚሰበስቡት የተቀማጭ ገንዘብ፣ ሃብትና የሚሰጡት ብድር በየአመቱ በአማካይ በ30 በመቶ እያደገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብ ከ189 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጸው ለባንኮች ተጨማሪ ሃብት ለማሰባሰብ እድል የሚፈጥር እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ባንኮች የሚከተሉት የብድር ፖሊሲ አጠቃላይ ልማቱን የሚደግፍና የግል ዘርፉን የሚያበረታታ እንዲሆን ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የፋይናንስ ተቋማት በአለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡት መመዘኛዎች መሰረት ስራቸውን እንዲያከናውኑ ጠንካራ የክትትል ስርአት ይዘረጋልም ብለዋል።

በተመሳሳይ የውጭ ዕዳን ለመቀነስና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የተጀመሩ የዕዳ ሽግሽግ ውይይቶች ይቀጥላሉ ብለዋል።

የተቀመጡ የትኩረት መስኮችን በማሳካት የማክሮ ኢኮኖሚውን አውድ ለማረጋጋት የፋይናንስ ተቋማት ትብብር አስፈላጊ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም