የንግድ ባንክ የካ ዲስትሪክት ሠራተኞች ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ136 ሺህ ብር ድጋፍ አደረጉ

286

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 24/2015 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካ ዲስትሪክት ሠራተኞች ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ136 ሺህ ብር ድጋፍ አደረጉ።

የባንኩ ሠራተኞች ለልብ ሕሙማን የበኩላቸውን ለማበርከት በማሰብ በዛሬው እለት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

በባንኩ የየካ ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ውብዓለም ከበደ፤ የዲስትሪክቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከልብ ታማሚ ህፃናት ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ የዛሬውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም የዲስትሪክቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ136 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። 

ለህፃናት ጤንነት ሁሉም የድርሻውን የማድረግና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ ካለን ላይ ቀንሰን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል። 

በመሆኑም ሌሎች ተቋማትም ለልብ ሕሙማን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ ሕሩይ ዓሊ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካ ዲስትሪክት ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።  

በባንኩ ሠራተኞች የተደረገው ድጋፍ የልብ ሕሙማን ህፃናትን ሕይወት ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም