ቀጥታ፡

ኢህአዴግ የተደራጀ ሌብነትንና ስርዓት አልበኝነትን እንደማይታገስ አስታወቀ

አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  (ኢህአዴግ) ከዚህ በኋላ የተደራጀ ሌብነትና ስርዓተ አልበኝነትን እንደማይታገስ አስታወቀ። ግንባሩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስራ ላይ ሪፎርም ማድረግ እንዳለበት መገምገሙም ተገልጿል። ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የኢህአዴግ 11ኛው ጉባኤ በዛሬ ውሎውም አገራዊ ለውጥን ማስቀጠል እንዲሁም የድርጅቱን በ10ኛው ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ትግበራ ሪፖርት ላይ ግመገማ እያደረገ ነው። የጉባዔው ቃል አቀባይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ግንባሩ ከዚህ በኋላ የተደራጀ ሌብነት፣ ዝርፊያ ስርዓት አልበኝነትን እንዲሁም ፍትሃዊ አገልግሎትን በአግባቡ መስጠት አለመቻልን አይታገስም። ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  በሊቀመንበሩ አማካኝነት በአገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎችና በውጭ አገሮች በመንቀሳቀስ የፈጠረውን አገራዊ አንድነት ጉባዔው በመልካምነት መገምገሙን ገልጸዋል። ግንባሩ በኢትዮጵያ ተከስቶ ከነበረው ሁከት ጋር ተያይዞ የአመራር ለውጥ በማካሄድ የፈጠረውን ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰዳቸው ርምጃዎች፣ በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ስኬቶች ጉባኤው በስፋት የገመገማቸው ሃሳቦች መሆናቸውን ተናግረዋል። የመረጃና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲሁም በሳይበር ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ጉባዔው ውይይት ያደረገባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል። አቶ ፍቃዱ፤ ግንባሩ በቀጣይ ፖለቲካዊና አስተዳደር ሪፎርሞች ላይ መስራት እንዳለበት በጉባዔው ላይ መነሳቱን አውስተዋል። ድርጅታዊ የመተጋገል ባህልን ማዳበር፣ ውስጠ ዴሞክራሲን ማጎልበት የተመለከቱ ነጥቦች በፖለቲካዊ ሪፎርም ላይ የተነሱ መሆናቸውን አክለዋል። አገሪቷ ካለችበት የእድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚሄድ አስተዳደራዊ የአሰራር ሪፎርም እንዲደረግ መገምገሙን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባም ጉባዔው መገምገሙን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም