የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ እስካሁን 2ሺህ8 የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አካሂዷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ እስካሁን 2ሺህ8 የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አካሂዷል
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ባለው የ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 2ሺህ8 የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ማካሄዱን ገለጸ። የዓይን ባንኩ በዛሬው እለት የተመሰረተበትን የ15ኛ ዓመት በአሉን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተገኙበት አክብሯል። የቀድሞው ፕሬዚዳት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የዓይን ባንኩ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በመጋፈጥ ከተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር በዓይን ብሌን ጠባሳ የተነሳ የዓይን ብርሃናቸው የጠፋባቸውን ወገኖች መታደግ ችሏል። የዓይን ባንኩ ከአስራ አምስት አመት በፊት ባንኩ ተመርቆ ሲከፈት በክብር እንግድነት መገኘታቸውን ገልጸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት በወቅቱ የአይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንደገቡ አስታውሰዋል። የዓይን ብሌን ልገሳ የሚካሄደው ከሞት በኋላ በመሆኑ ሁሉም ወገን ብርሃን ከመቅበር የዓይን ብሌኑን ቢለግስ ለሌሎች ብርሃን የሚሰጥ በመሆኑ የዓይን ብሌኑን ለመለገስ ቃል መግባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የዓይን ባንኩ ስራ አስኪያሥጅ ወይዘሮ ለምለም አየለ በባንኩ በኩል የሚሰጠው የአይን ብሌን ንቀለ ተከላ አገልግሎት ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። የዓይን ባንኩ የሚችለውን ያህል እየሰራ ቢሆንም በኢትዮጵያ ካለው የዓይን ብሌን ጠባሳ ችግር አንጻር በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ይህም ሊሆን የቻለው ህብረተሰቡ በዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ የሌለው በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል። በቀጣይ አገልግሎቱን ለማሳደግ በቂ የዓይን ብሌን ለጋሾችን ቁጥር ለመጨመር ከሀይማኖት ተቋማትና ከእድሮች ጋር ለመስራት እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ወይዘሮ ለምለም ገልጸዋል። ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል ከገቡት መካከል ሲሆን ፣ አይኑን በመለገሱ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው ገልጿል። ''ከዚህ አለም በሞት ስንለይ ብሌናችን በሌሎች ውስጥ ብርሃንን በመለገስ በምንሰጠው አገልግሎት እንደገና ረዥም እድሜን መኖር እንችላለን'' ብሏል። እስካሁን በዓይን ባንኩ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ ከህልፈታቸው በኋላ 15ሺህ ወገኖች የአይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል። የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የሚሰበስባቸውን የዓይን ብሌኖች ንጽህናቸውን በማረጋገጥ፣ በአዲስ አበባ ለዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ለብሩህ ቪዥን ልዩ የዓይን ክሊኒክና ለዋጋ ልዩ የዓይን ክሊኒክ በማሰራጨት የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንዲካሄድ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። እንዲሁም ባንኩ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ኩሃ ሆስፒታል፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ሀዋሳና አርባምንጭ ዩንቨርሲቲ ሆስፒታሎችና በብሌን ልዩ የዐይን ክሊኒክ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተገልጿል። የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሰኔ 21 ቀን 1995 ዓ.ም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና በኦርቢስ ኢንተርናሽናል የግብረሰናይ ድርጅት የሶስትዮሽ ስምምነት በጋራ የተመሰረተ ነው።