በውጭ ጉዳይና በብሄራዊ ደህንነት ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጥ ሁለተኛው ጆርናል ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ጉዳይና በብሄራዊ ደህንነት ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጥ ሁለተኛው ጆርናል ተመረቀ
ሀዋሳ መስከረም 24/2011 በውጭ ጉዳይና በብሄራዊ ደህንነት ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጥ ሁለተኛው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ኢንስትቱዩት ጆርናል ተመረቀ፡፡ ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆነው ኢንስትቱዩት በውጭ ፖሊሲዎችና ዲፕሎማሲዎች ዙሪያ የተለያየ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡ በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጆርናልም ያሳትማል፡፡ ''የአፍሪካ ቀንድ ዝመቶችና ንቃቂቶች'' የሚል የመጀመሪያውን ጆርናል በመስከረም 2010 ያሳተመ ሲሆን፣ በአባይ ሸለቆና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ሁለተኛው ጆርናል ሰሞኑን በሃዋሳ አስመርቋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ኢንስትቱዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የጆርናሉ ዓላማ ተመራማሪዎችና የፖሊሲ አውጪዎችን ለማገናኘትና የዕውቀት ሽግግር ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ''ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን የሃሳብ ጉባዔነት ራዕይ ማሳካት ይችላል'' ብለዋል፡፡ የአገሪቱ የውሃ ሃብት የኢትዮጵያና የግብፅ ብቻ ሳይሆን ፤ የአካባቢያዊና ሰብዓዊ ደህንነት ጉዳይ ተመራማሪዎችንና ፖሊቲከኞችን ትኩረት መሳቡን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ ጆርናሉ የህግ ማዕቀፎችን የሚፈትሹ ጥናቶችና ምርምሮችን መረጃ ለማስተላለፍ ተብሎ መታተሙን አስታውቀዋል፡፡ የጆርናሉ አርታኢ አቶ ዳደ ደስታ እንዳሉት በጆርናሉ አባይን የተመለከቱ ጉዳዮች በዋነኝነት ለመቃኘት ተሞክሯል፡፡ ጆርናሉ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ፣ በሱዳን፣ በእሥራኤልና በምዕራብ አውሮፓ አገሮች የሚገኙ የሃይድሮ-ፖሊቲክስና ጂኦ-ፖሊቲክስ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ የህግ ባለሙያዎች፣ የፖሊቲካና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሳይንቲስቶች፣ የማህበራዊ ጂኦግራፊ ሊቆችና ታዋቂ ጸሐፍትን አሳትፏል። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንግሊዛውያን በጣና ላይ ግድብ ለመገንባት ያደረጉትን ያላሰለሰ ጥረትና ተያያዥ ጉዳዮች ያካተቱበትን ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ ፕሮፌሰር ኤርሊክ ሃጋይ የናይል ጉዳይና ታሪካዊ ግጭቶች፣ ዶክተር ደረጀ ዘለቀ የራስጌና የግርጌ አባይ አገሮች የምስጢር አጀንዳዎችን አቅርበዋል፡፡ የፕሮፌሰር ተስፋይ ታፈሰ፣ የሳልማን መሃመድ ሳልማን፣ የክርስቲን ቻርሎት እንዲሁም የሱዳንና የግብፅ ፕሮፌሰሮች ሃሳቦችና ዲስኩሮችም ታትመውበታል፡፡ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ያበረከቱት ጽሁፍም ተካቶበታል፡፡ ዕትሙ መታሰቢያነቱን ለቀድሞው የታላቁ የኢትዮጰያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አድርጓል፡፡